የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል ሳዑዲ አረቢያ ወደ ለዘብተኛ የእስልምና ስርዓት መመለስ ትፈልጋለች አሉ።

የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን እና የዓለመ አቀፉ የገንዘብ ፈንድ ዳይሬክተር ክርሰቲያን ላጋርድ።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን ይህን አስተያየት የሰጡት በሪያድ ሲካሄድ በነበረው የኢኮኖሚ ስብሰባ ላይ ነው።

የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን፤ ሳዑዲ አረቢያ ወደ 'ለዘብተኛ የእስልምና ስርዓት መመለስ' የባህረ ስላጤዋን ሃገር ለማዘመን ቁልፍ ነው ብለዋል።

ልዑሉ በሰጡት መግለጫ ከአጠቃላይ የሳዑዲ ዜጎች ሰባ በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከሰላሳ ዓመት በታች መሆኑን ጠቁመው፤ እነዚህ ወጣቶች ''ሃይማኖታችን መቻቻል ሲል የሚገልፀውን'' አይነት ህይወት ይሻሉ ብለዋል።

አልጋ ወራሹ ''አክራሪ የእስልምና ስርዓት አራማጆችን በቅርቡ አስወግዳለሁ" ሲሉም ቃል ገብተዋል።

ይህ ሃሳባቸውን የተናገሩት በ500 ቢሊያን ዶላር ኢንቨስትመንት የምትገነባውን ከተማ እና የንግድ ቀጠና ካስተዋወቁ በኋላ ነበር።

ኒዮም ተብላ የተሰየመችው ከተማ፤ በ26500 ስኩዌር ኪ.ሜ ላይ የምታርፍ ሲሆን በሳዑዲ አረቢያ ሰሜን-ምዕራብ አቅጣጫ ለግብፅ እና ለዮርዳኖስ ቅርብ በሆነ ቦታ ላይ ትገነባለች።

ባለፈው ዓመት የ32 ዓመቱ አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሃመድ በነዳጅ ላይ የተመሰረተውን የሳዑዲ ኢኮኖሚ ለመቀየር ባለ ብዙ ዘርፍ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ለውጦችን ለማምጣት ራዕይ 2030 የተባለውን እቅድ አስተዋውቀው ነበር።

በዚህ እቅድ ውስጥ የተለያዩ ማሻሻያዎች የተካተቱ ሲሆን በሳውዲ መንግሥት ስር የሚገኘውን ሳዑዲ አርማኮ የተባለውን ነዳጅ አውጪ ኩባንያን በከፊል ወደ የግል ይዞታ ማዞር ይገኝበታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የሳዑዲ ኢኮኖሚ የተመሰረተው በተፈጥሮ የነዳጅ ሃብቷ ላይ ነው

ምንም እንኳን ከወግ አጥባቂዎች ተቃውሞ ቢሰነዘርም፤ ከወር በፊት የልዑሉ አባት ንጉስ ሰልማን ሴቶች መኪና ማሽከርከር እንዲችሉ መወሰናቸው ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት በመዝናኛ ዘርፉ መዋዕለ ንዋዩን ፈሰስ ማድረግ ይፈልጋል። ኮንሰርቶች በድጋሚ በሳዑዲ መደረግ ይጀመራሉ፤ ሲኒማ ቤቶች እንደገና ይከፈታሉ ተብሏል።

አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሃመድ እቅዳቸውን በሪያድ ይፋ ባደረጉበት ወቅት የበርካታ ባለሃብቶችን እና የሃገር ተወካዮችን ቀልብ መሳብ ችለዋል።

''ለተቀሩት ሃይማኖቶች፣ ባህሎች እና ከተለያዩ ዓለማት ለሚመጡ ሰዎች ክፍት ወደሆነው እና ከዚህ በፊት ወደ ነበርንበት- ለዘብተኛ የእስልምና ስርዓት ነው የምንመለሰው'' ብለዋል።

''ሰባ በመቶ የሚሆኑት ዜጎቻችን ከሰላሳ ዓመት በታች ናቸው። በሚቀጥሉትን ሰላሳ ዓመታት አፍራሽ የሆኑ ሃሳቦችን ማራመድ አንችልም። ምክንያቱም ይህ አካሄድ ወጣቱን በአንድ ጊዜ ሊያጠፋ ይችላል።''

አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሃመድ ''ሳዑዲ አረቢያ እአአ ከ1979 በፊት እንደዚህ አልነበረችም'' ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል።

በኢራን በነበረው እሰላማዊ አብዮት እና ታጣቂዎች የመካን ትልቁን መስኪድ ከተቆጣጠሩ በኋላ ህዝባዊ መዝናኛዎች በሳውዲ ተከለከሉ እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች በዜጎች ህይወት ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንደጀመሩ ይነገራል።