የካታሎን ነፃነት መሪ በቤልጂዬም ጥገኝነት እንደማይጠይቁ አሳወቁ

Carles Puigdemont also said he would respect snap elections in December

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በቅርቡ በስፔን መንግሥት የተባረሩት የካታሎንያ ፕሬዚደንት ካርልስ ፒዩጄሞንት ሃገራቸውን ጥለው ወደ ቤልጂዬም ያቀኑት ጥገኝነት ለመጠየቅ እንዳልሆነ አሳውቀዋል።

ቤልጂየም ብራሰልስ ውስጥ ይፋ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ፒዩጄሞንት ከፍትሕ ለማምለጥ እየሞከሩ እንዳልሆነ፤ ነገር ግን በነፃነት ሃሳባቸውን ለመግለፅ እንደሚሹ አሳውቀዋል።

አክለውም በአውሮፓውያኑ ታህሳስ 21 ሊካሄድ የታሰበውን የካታሎንያ ነፃነት ምርጫ ውጤትን እንደሚቀበሉም ተናግረዋል።

"ከማዕከላዊ መንግሥት ግልፅ የሆነ ቁርጠኝነት እፈልጋለሁ። የስፔን መንግሥት አብዛኛው ካታሎንያዊ ለመገንጠል ድምፁን ሲሰጥ ይቀበል ይሆን?" ሲሉም ጠይቀዋል።

የስፔን መንግሥት በካታሎንያ ነፃነት እንቅስቃሴ መሪዎች ላይ የአመፅ ማነሳሳት ክስ እንዲመሠረትባቸው ያዘዘ ሲሆን የነፃነት ሕዝበ-ውሳኔውም ውድቅ እንዲሆን አዟል።

አልፎም የስፔን ማዕከላዊ መንግሥት ዕለተ ሰኞ ካታሎንያን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረ ሲሆን ነባር ባለሥልጣናትን በማባረር በምትካቸው ሌሎችን ሹሟል።

ባለፈው ሳምንት የካታሎንያ ፕሬዚደንት ካርልስ ፒዩጄሞንት ያወጁት ነፃነት ሙሉ በመሉ ውድቅ ሆኖ በምትኩ አዲስ ምርጫ እንዲከናወንም ታዟል።

ማክሰኞ ዕለት የስፔን ፓርላማዊ ኃይል ከነፃነት እንቅስቃሴው ጋር ግኑኝነት አላቸው የተባሉ ስምንት የካታሎንያ መሪዎችን ቢሮ ሰባብሮ በመግባት ፍተሻ ማከናወኑም ይታወሳል።

የስፔን መንግሥት የካታሎንያ ፖሊስ ኃይልን ፓርላማዊ ኃይሉ ነፃነቱን ደግፈው የወጡ ሰልፈኞችን በሚመክትበት ወቅት አልተባበረም በሚል ወቅሷል።

መሪው ቤልጂዬም ምን ይሰራሉ?

ብራሰልስ የሚገኙት ፒዩጄሞንት ለምን ያህል ጊዜ በቤልጂዬም ዋና ከተማ እንደሚቆዩ አልገለጡም፤ ሆኖም የስፔን መንግሥት ማረጋገጫ ከሰጣቸው ወደሃገራቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ጠበቃቸውም "እዚህ የመሆን ሙሉ መብት አላቸው። ማንም በዚህ አቋማቸው ሊቃወማቸው አይችልም" ሲሉ አሳውቀዋል።

የካታሎንያው መሪ በብራሰልስ ጥገኝነት ይጠይቃሉ ወይ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ "ሁሉንም ዓይነት ምርጫዎች ለመጠቀም ዝግጁ ነን። ውሳኔ ላይ ግን አልደረስንም" በማለት የፒዩጄሞንት ጠበቃ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።

የስፔን ፍርድ ቤት የካታሎንያ ነፃነት መሪዎች በአመፅ በማነሳሳት እና የመንግሥት ገንዘብ ያለአግባብ በማባከን ከሷቸዋል።

የካታሎንያ ፕሬዚደንት ካርልስ ፒዩጄሞንት በክሱ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስክ ሰላሳ ዓመት እስራት ድረስ ሊቀጡ እንደሚችሉ ተነግሯል።