በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ሁለት ምርጫ ያከናወነችው ኬንያ ቀጣይ ዕጣ. . .

Image copyright AFP

በኬንያ የገዢው ፓርቲ ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆነው ናሳ መሪ ራይላ አዲንጋ ዛሬ የዳግም ምርጫውን ተከትሎ በቀጣይ ስላሰቧቸው እርምጃዎችና መሰል ጉዳዮች መግለጫ ሰጥተዋል።

አሁሩ ኬንያታ 98 በመቶ ድምፅ በማምጣት ያሸነፉበትን ውጤት በሕግ እንደሚፋረዱ የተጠበቁት ኦዲንጋ ስለጉዳዩ ምንም ዓይነት ፍንጭ አልሰጡም።

ቢሆንም የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉ አስረግጠው የተናገሩ ሲሆን፤ ሰላማዊ የሆነው ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉበትም ተናግረዋል።

ተቃዋሚ ፓርቲው ምርጫውን ውጤት በተመለከተ ክስ ለመመስረት የስድስት ቀናት ዕድሜ ሲኖረው የምርጫውን መካሄድ አስመልክቶ ከዚህ በፊት የቀረበው ክስ ዳኞች ባለመሟላታቸው ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወሳል።

ኬንያ ውስጥ ምርጫ የሹመት ሥነ-ሥርዓት እየሆነ መጥቷል ያሉት ራይላ ኦዲንጋ፤ ምርጫውን የሚያከናውነው አካል ነፃና ገለልተኛ አይደለም በማለት ራሳቸውን ከድጋሚ ምርጫው ማግለላቸው ይታወሳል።

በአጠቃላይ በምርጫው ለመሳተፍ ከተመዘገበው ሕዝብ 39 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው በዳግም ምርጫው የተሳተፈው።

ኦዲንጋ 'የሕዝብ ጉባዔ' ያሉትን አካል በማቋቋም ምርጫው ነፃ እና ፍታሃዊ እንዳልነበር እንደሚያጣሩም አሳውቀዋል።

አልፎም ኦዲንጋ ዳግም ምርጫውን በ98 በመቶ ድምፅ ያሸነፉትን ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታንና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶን ወርፈዋል።

"ሁለት ሥልጣን የጠማቸው ግለሰቦች ነፃነታችንና ዲሞክራሲያችንን ሲያጠፉት ቁጭ ብለን አንመለከትም" ብለዋል።