ኒው ዮርክ ውስጥ በመኪና በደረሰ ጥቃት ስምንት ሰዎች ተገደሉ

Photo allegedly showing suspect

የፎቶው ባለመብት, CBS

በኒውዮርክ የታችኛው ማንሃተን የብስክሌተኞች መንገድ ላይ አንድ ግለሰብ በተሽከርካሪው ቢያንስ ስምንት ሰዎችን ሲገድል አስራ አንዱ ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት አድርሷል።

የ29 ዓመቱ ግለሰብ ከመኪናው ሲወርድ በፖሊስ ተመትቶ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ኃላፊዎች ጥቃቱ የሽብር ድርጊት መሆኑን አስታውቀዋል።

ጥቃቱን ያደረሰው ሳይፉሎ ሳይፖቭ የተባለ እና እ.አ.አ በ2010 ወደ አሜሪካ የመጣ ስደተኛ መሆኑን የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የጸጥታ አስከባሪ አካላት ለሲቢሲ ዜና ክፍል እንደገለጹት ግለሰቡ መኪና ውስጥ ከአይ ኤስ ጋር የሚገናኝ ጽሑፍ ተገኝቷል።

ግለሰቡ ወደ ሆስፒታል መወሰዱ ተዘግቧል።

"በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመ የሸብር ጥቃት ነው" ሲሉ የኒው ዮርክ ከንቲባ ቢል ደ ብላሲኦ ገልጸዋል።

"መንፈሳችንን ለመስበር የተፈጸመ ድርጊት ነው። ሆኖም የኒው ዮርክ ነዋሪዎች ጠንካራ መሆናችንን እናውቃለን። መንፈሳችንም በረብሻ እና በማስፈራራት የሚዳከም አይደለም" ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ድረ-ገጻቸው ላይ በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው እና ለቤተሰቦቻቸው መጽናናት ተመኝተዋል።

"ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ከባድ ጉዳት ቢያስተናግዱም ለህይወታቸው የሚያሰጋ አይደለም" ሲሉ የኒው ዮርክ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀምስ ኦኒዬል ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

"የሞቱትና አካል ጉዳት ደረሰባቸው ዕለት ከዕለት ስራቸውን በማከናወን ላይ የነበሩ ናቸው" ብለዋል።

"ጥቃቱ ለብዙ ሰዎችና ቤተሰቦች ትልቅ ሃዘን የፈጠረ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢ ብዙ ብስክሌቶች ተበታትነው ታይተዋል።

አንድ የዓይን እማኝ ለኤቢሲ ቻናል 7 እንደገለጸው ከሆነ በከፍተኛ ፍጥነት የሚሽከረከር መኪና በብስክሌት መንገድ ላይ ሰዎችን እየገጨ ሲሄድ እንዳየ ተናግሯል።

ዘጠኝ ወይም 10 የሚሆን የጥይት ድምጽ እንደሰማም ተናግሯል።

ሌላ እማኝ በበኩሉ አንድ ግለሰብ ሲሮጥ መመልከቱን እና ከአምስት እስከ ስድት ጊዜ የተኩስ ድምጽ መስማቱን ለኤን ዋይ 1 ቴሌቪዥን ተናግሯል።

"በእጁ የሆነ ነገር ይዞ እንደነበር አይቻለሁ። ምን እንደሆነ ግን አላወቅኩም። እነሱ ግን የጦር መሳሪያ ነው ብለዋል" ሲል ገልጿል።

"ፖሊሶች ሲተኩሱበትም መሮጡን አላቆመም። አካባቢው ተተራመሰ። በድጋሚ ስመለከት ሰውየው ወድቋል" ሲል ተናግሯል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ኋይት ሃውስ አስታውቋል።