ያልተፈታው የካታሎንያ እንቆቅልሽ

ሰዎች የካታላንን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ህዝበ ውሳኔውን የሚደግፉና የሚቃወሙ ሰዎች በየፊናቸው ሰልፍ እየወጡ ነው

ከስልጣን የተነሱትን የካታሎንያ መሪ ካርለስ ፑይደሞንትን ጨምሮ የተበተነው መንግሥታቸው አባላት የሆኑ 13 ሰዎች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የስፔን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አስተላለፈ።

ለደረሱ ጉዳቶችም 7.2 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ሶስት ቀናት ተሰጥቷቸዋል።

ባለፈው ሰኞ የስፔን ከፍተኛ አቃቤ ህግ "በአማጺያኑ" ላይ ክስ እንደሚከፍት ከገለጸ በኋላ ነበር ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ያወጣው።

ፑይደሞንት እና የተወሰኑ ሚንስትሮቻቸው በቤልጂየም የሚገኙ ሲሆን ፑይደሞንት ጥገኝነት እንደማይጠይቁ ተናግረው ነበር።

ካርለስ ፑይደሞንት በካታላኖንያ የነጻነት ህዝበ ውሳኔ በማካሄድ ቀውስ የቀሰቀሱ ሲሆን የሃገሪቱ ህገመንግሥታዊ ፍርድ ቤት ምርጫን ውድቅ አድርጎታል።

አሁን የስፔን መንግስት ካታላኖንያን በቀጥታ ተቆጣጥሯል።

ፑይደሞንት እና ሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸው በይፋ ባይከሰሱም ፍርድ ቤት የማይቀርቡ ከሆነ አቃቤ ህጎች እንዲታሰሩ ትዕዛዝ ሊያወጡ ይችላሉ።

ፍትሃዊ የፍርድ ሂደት ካለ ወደ ስፔን እንደሚመለሱ ፑይደሞንት መናገራቸው ይታወሳል።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ካርለስ ፑይደሞንት በመጪው ጥር የሚካሄደውን ምርጫ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል

በስፔን የሚገኙ ብዙዎቹ የፑይደሞንት የቀድሞ የስራ ባልደረቦች ፍርድ ቤት ለመቅረብ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል።

በአማጺያኑ ላይ እስከ 30 ዓመት የሚደርስ እስር ሊፈረድባቸው ይችላል።

ቀጣዩ ምርጫ

ፑይደሞንት ወደ ቤልጂም ያቀኑት የፍርድ ቤት ቅጣትን ለማምለጥ ሳይሆን በነጻነት ለመናገር መሆኑን ባለፈው ማክሰኞ አስታውቀው ነበር።

የካታሎንያ ፓርላማ ባለፈው አርብ ያወጀውን ነጻነት የስፔን ህገመንግሥታዊ ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎታል።

በመጪው ታህሳስ በስፔን መንግሥት እንዲካሄድ የታቀደውን ምርጫ እንደሚቀበሉት ፑይደሞንት አስታውቀዋል።

"ከመንግሥት ቁርጠኛ ውሳኔ እፈልጋለሁ። መንግሥት ለተገንጣዮች የሚሰጠውን ከፍተኛ ምርጫ ድምጽ ይቀበላል?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

የስፔን መንግሥት አዲስ በሚካሄደው ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

በሌላ በኩል ጋርዲያ ሲቪል የተባለው የስፔን ጦር ሃይል የካታሎንያ ፖሊስ ሃይልን ወሯል።

እንደመገናኛ ብዙሃን ከሆነ ጦሩ ካለፈው የነጻነት ህዝበ ውሳኔ ጋር የሚገናኙ መረጃዎችን ለማግኘት ስምንት ቢሮዎችን ፈትሿል።

ተያያዥ ርዕሶች