አመጹን ተከትሎ በአስመራ ወጣቶች እየታሰሩ ነው

አስመራ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በአስመራ ከተማ የምትገኘውና በትናትናው ዕለት አመጽ የተነሳባት አኽርያ ተብላ የምትጠራው ስፍራ በወታደሮች ጥበቃ ስር መሆኗንና አብዛኛው ህዝብ ፈርቶ ከቤቱ እንዳልወጣ፤ እንዲሁም ዛሬ አንዳንድ ወጣቶች "ተጠይቃችሁ ትመለሰላቸሁ" እየተባሉ እንደታሰሩና ሽማግሌዎች ግን እንዳልተነኩ ምንጮቻችን ተናግረዋል።

የግጭቱ መነሻ?

በዚህ ዓመት መስከረም ወር አጋማሽ ላይ ደያእ አል ኢስላም የተባለው ትምህርት ቤት በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ እንዲካተት የሚገልፅ መልዕክት ደርሶት ነበር።

የትምህርት ቤቱ የወላጆች ኮሚቴ በሕዝብ ገንዘብ የተገነባው ት/ቤት የሕዝብ እንጂ መንግሥት ሊወርሰው አይገባም በማለት እንደተቃወሙና በጉዳዩ ላይ ውይይት እንደተደረገበት ይነገራል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ተካሂዶ በነበረው የወላጆችና ተማሪዎች ስብሰባ ላይ የተቀረፀው ድምፅና ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያስረዳው ሃጂ ሙሳ መሃመድ የተባሉ የት/ቤቱ አስተዳዳሪ "ያመጣችሁትን ሐሳብ አልደግፈውም፤ ከሐሳባችን ጋር የማይገናኝና ተቀባይነት የሌለው ነው'' ሲሉ ተቃውመው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ በእስልምና አስተምህሮት ሊመራ እንደሚገባ የገለፁት ሃጂ "ተሸፍነው የሚመጡት ሴት ተማሪዎች ልጆቻችን ናቸው። የሚነካቸው የለም። ስለዚህ ለሚመጣው ነገር ሁሉ ዝግጁ ነን። ምክንያቱም ሃይማኖቱን እና ሥነ-ምግባሩን ለመጠበቅ የማይሞት የለም" ብለዋል።

እኚሁ የ93 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ቀጥለው "ይህ ትምህርት ቤት በሕዝብ ገንዘብ ነው የተገነባው። ሃይማኖት ደግሞ ከመጥፎ ተግባር አርቆ ወደ በጎነት የሚመራ ነው። እኛ ሙስሊሞች ነን። ሃይማኖታችን በሚፈደቅድልን የሸሪዓ ህግ ደግሞ እንመራለን" በማለት ሃሳባቸውን ገልፀዋል።

ይህንን ተከትሎ ተናጋሪው ሃጂ ሙሳ መሃመድ ለእስር እንደተዳረጉም ታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

ከሃጅ መሃመድ እስር በኋላም ቁጥራቸው ወደ አንድ መቶ የሚጠጋ ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሲሆን "አባታችንን ፍቱልን፤ ት/ቤታችንን መልሱልን" የሚል መፈክር ይዘው ነበር። ሰልፈኞችን ለመበተን አድማ በታኞች ወደ ሰማይ ጥይት የተኮሱ ሲሆን ሰልፉም ወዲያው ተበትኗል።

ትናንት ከሰዓት በኋላ በወጣቶች በተነሳ አመጽ ምክንያት በአስመራ ከተማ ተኩስ እንደተሰማ ምንጮች እንደገለፁ የሚታወስ ነው።

ከአመጹ በኋላ በኤርትራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞቹ ውጥረት ወደተስተዋለባቸው የአስመራ አከባቢዎች እንዳይንቀሳቀሱ አሳስቧል።

በተለያዩ ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል የተኩስ ድምጽ እና ሰዎች ራሳቸውን ለማዳን ሲሮጡ በግልጽ ያሳያል። ሆኖም ግን ተኩሱ ምን ዓይነት አደጋ እንዳስከተለ የታወቀ ነገር የለም።

የኤርትራ መንግሥት ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በቲዊተር ገጻቸው በሳፈሩት ሓሳብ ብጥብጡ እንደተከሰተ ሆኖም ግን ምንም ችግር ሳያስከትል መበተኑን ገልጸዋል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ኤርትራ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር የደወለ ቢሆንም ሚኒስትሩ ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል ምክንያት መረጃ ሊያገኝ አልቻለም። ናይሮቢ ከሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል።

በኤርትራ የጣልያን ኤምባሲ ሰራተኛ የሆኑት ዲየጎ ሶሊናስ በበኩላቸው ሁከቱ ትናንት ከሰዓት በኋላ መከሰቱን እና በአጭር ግዜ ውስጥ እንደተበተነ በመግለጽ አሁን ላይ ሁኔታው እንደተረጋጋ ገልጸዋል።

በአንጻሩ አስመራ የሚገኙ ምንጮቻችን አኽርያ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጥብቅ ቁጥጥር ስር እንደሆነ እና ሰዎች መታሰራቸውን ገልጸውልናል።