የላይቤሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድጋሚ ምርጫ እንዳይካሄድ አገደ

George Weah (L) and Joseph Boakai (R)

የፎቶው ባለመብት, Reuters/ EPA

የምስሉ መግለጫ,

የቀድሞው እግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ እና ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ጆሴፍ ቦአካይ መካከል ነበር ድጋሚ ምርጫው ሊካሄድ ቀን የተቆረጠው

በመጀመሪያው ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማጭበረበሮች ነበሩ የሚሉ ቅሬታዎች ከመጡ በኋላ የላይቤሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለዳግም ምርጫ የሚደረገው ዝግጅት እንዲቋረጥ አግዷል።

በቀድሞው እግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ እና ምክትል ፕሬዝዳንት በሆኑት ጆሴፍ ቦአካይ መካከል ነበር ድጋሚ ምርጫው በመጪው ማክሰኞ ሊካሄድ ዕቅድ ተይዞ የነበረው።

ሆኖም በመጀመሪያው ዙር ሶስተኛ የወጡት ቻርለስ ብሩምስኪን ውጤቱ ተገቢ አይደለም በሚል ከሰዋል።

ውሳኔውን ተከትሎ አድማ በታኝ ፖሊሶች ፍርድ ቤቱንና የምርጫ ኮሚሽኑን ሲጠብቁ ታይተዋል።

ከአፍሪካ ህብረትና ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ ተወካዮች ወደ ሃገሪቱ ያቀኑ ሲሆን ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ያነጋግራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሬዝዳንቷ ማንን ይደግፋሉ?

ብሩምስኪን እና ሊበርቲ ፓርቲ የምርጫ ጣቢያዎች ቀድመው በመዘጋታቸው መራጮች እንዳይመርጡ ከመደረጉም በላይ ብዙ ማጭበርበሮች የተካሄዱበት ነበር ሲሉ የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ያጣጥላሉ።

ይህንን ተከትሎም ዳግም ምርጫው የቀረበው ክስ በትክክል እስኪጣራ ድረስ ይራዘማል ብሏል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ከማስተላለፉ በፊትም፤ ታዛቢዎች ለምርጫ ኮሚሽኑ ድጋሚ ምርጫውን ለማካሄድ በቂ ጊዜ አልተሰጠውም እያሉ ነበር።

ከሊበርቲ ፖርቲ በተጨማሪ የቦአካይን ዩኒቲ ፓርቲን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ፓርቲዎችም ምርጫው ላይ ቅሬታ አቅርበዋል። የዩኒቲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጭምር በምርጫው ላይ ጣልቃ ገብተዋል ብለዋል።

በምርጫ አሸንፈው ስልጣን በመያዝ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንትና የኖቤል የሠላም ዘርፍ አሸናፊ የሆኑት ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የምርጫ ውጤቱ ጣልቃ ሳይገቡ እንዳልቀሩ ጥርጣሬዎች አሉ።

በኤለን ጆንሰን እና በምክትላቸው መካከል ጥሩ ግንኙነት እንደሌለ የሚገልጹ ሰዎች ምክትል ፕሬዝዳንቱ እንዲተኳቸው አይፈልጉም ሲሉም ይገልጻሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty

የምስሉ መግለጫ,

ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ምክትላቸውን አልደገፉም በሚል ቅሬታ እየቀረባበቸው ይገኛል

ኤለን ጆንሰን ግን በተደጋጋሚ ጊዜ በመጀመሪያው ዙር 28.8% ድምጽ በማግኘት ሁለተኛ የወጡትን ቦአካይን እንደሚደግፉ ተናግረዋል። በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ጆርጅ ዊሃ 38.4% ድምጽ በማግኘት ቀዳሚ ሆነዋል።

"ለ12 ዓመታት በስልጣን ላይ ለቆየ ፓርቲ ይህን መሰሉ ለቅሶ የሚያሳዝን ነው" ሲል የዊሃው ኮንግረስ ፎር ዴሞክራቲክ ቼንጅ ፓርቲ አስታውቋል።

ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሁሉም አካላት ሠላማዊ በመሆን ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ታዛቢዎች ከአንዳንድ ችግሮች በስተቀር የጎላ ነገር አለማየታቸው እንዳስታወቁ ኤ ኤፍ ፒ ዘግቧል።

ፍርድ ቤቱ ሊበርቲ ፓርቲ እና የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን በመጪው ሐሙስ ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸውን እንዲያስታውቁ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የምርጫ ኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሄነሪ ፍሎሞ ኮሚሽኑ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት እንደሚሰራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።