ለብዙዎች ወርቃማ እድል የሆነው የዲቪ ሎተሪ

Diversity Visa Lottery

የፎቶው ባለመብት, JIM WATSON

በየዓመቱ 14 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በወርሃ ጥቅምት ላይ የሚጀመረውን የዲቪ ሎተሪ ተጠቅመው ህጋዊ የአሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ይመዘገባሉ።

ግሪን ካርድ ሎተሪ የሚባለውን ፕሮግራም ተጠቅመው እ.አ.አ ከ1995 ጀምሮ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ቪዛ አግኝተዋል።

ትላንት በኒው ዮርክ ጥቃት ያደረሰው ግለሰብ በ2010 የግሪን ካርድ ፕሮግራም ባለዕጣ ሆኖ ወደ አሜሪካ መግባቱን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፕሮግራሙን አጣጥለዋል።

ባለፈው ጥር የግሪን ካርድ ሎተሪ በችሎታ፣ በትምህርት እና በመሰል የመምረጫ ሂደቶች መሰረትነት ወደሚሰጥ ዘዴ እንዲቀየር ሪፐብሊካኖች ያቀረቡትን ዕቅድ ፕሬዝዳንቱ ደግፈዋል።

የዲቪ ሎተሪው ምንድን ነው?

የዲቪ ሎተሪ ፕሮግራሙ በአሜሪካ በስደተኝነት በቂ ድርሻን ላላገኙ ሃገራት ዜጎች በየዓመቱ 50 ሺህ ቪዛዎችን ይሰጣል። ይህ ደግሞ የአሜሪካ ዜግነትን ለማግኘትም በር ከፋች ነው።

የምርጫው ሂደት በኮምፒውተር ሲሆን ቪዛ ተቀባዮች አሜሪካ ውስጥ ስፖንሰር፣ ሥራ ወይም ደግሞ ቤተሰብ እንዲኖራቸው አይጠበቅባቸውም።

እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ ሜክሲኮ፣ ህንድ እና ቻይናን ጨምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት50 ሺህ የግሪን ካርድ የዲቪ ሎተሪ አሸናፊዎች ያሏቸው ሃገራት ዜጎች በእድሉ መሳተፍ አይችሉም።

በሎተሪው ላይ ለመሳተፍ ብቸኛው መስፈርት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቅ ወይም ከዚህ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የትምህርት ደረጃ መያዝ ነው።

አሸናፊዎች የትዳር አጋሮቻቸውን እና ታዳጊ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ አሜሪካ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው ሲሆን ይህ ግን በፕሬዝዳንት ትራምፕ ድጋፍ አልተሰጠውም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዲቪ ሎተሪ ዕጩዎች በአሜሪካ ኤምባሲ በመገኘት ፊት ለፊት ቃለ መጠየቅ ማድረግ ይኖርባቸዋ።

ከሽብር ጋር በተያያዘ ሪከርድ ያለባችወ አመልካቾች ዕድሉ የማይሰጣቸው ይሆናል።

በዕድሉ ማን ተጠቀመ?

ህጉ መጀመሪያ ላይ የአውሮፓ ስደተኞችን ቁጥር ለማብዛት ተብሎ ቢጀመርም የስደተኞችን ቁጥር ከመጨመሩም በላይ በተለይ ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ የሚገቡትን ሰዎች ቁጥር አሳድጎታል።

እንደፒው ሪሰርች ሴንተር ጥናት ከሆነ የሎተሪ ፕሮግራሙን በመጠቀም ከሰሃራ በታች ያሉ አፍሪካ ሃገራት ወደ አሜሪካ ለመግባት ችለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ዕገዳ እንዲጣልባቸው ከሚፈልጓቸው ሃገራትም ፕሮግራሙን ተጠቅመው ወደ አሜሪካ የገቡ አሉ።

እንደ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከሆነ እ.አ.አ በ2015 ኋይት ሃውስ በጥቁር መዝገብ እንዲሰፍሩ ከሚፈልጋቸው ስድስት የሙስሊም ሃገራት ብቻ 10,500 ሰዎች ለዲቪ ቪዛ ሎተሪ ተመርጠዋል።

ትራምፕ የግሪን ካርድ ሎተሪን ያስቀራሉ?

ፕሬዝዳንቱ በራሳቸው ፕሮግራሙን የማስቀረት ስልጣን የሌላቸው ሲሆን የአሜሪካ ኮንግረስ አዲስ የስደተኞች ህግ እስኪያወጣ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

ትራምፕ በሃገሪቱ ሴኔት ውስጥ በወግ አጥባቂዎች ድጋፍ ያገኘውና ግሪን ካርድን ለማስቀረት የቀረበውን ዕቅድ ይደግፋሉ። ዕቅዱ የስደተኞችን ቁጥር በግማሽ ይቀንሳል ተብሏል።

ሪፎርሚንግ አሜሪካን ኢሚግሬሽን ፎር ስትሮንግ ኢምፕሎይመንት አክት የተባለው ዕቅድ እ.አ.አ. ጥር 2017 ይፋ የተደረገ እና በፕሬዝዳንት ትራምፕ ድጋፍ የተሰጠው ቢሆንም በሴኔቱ ማግኘት የሚገባውን ያህል ድምጽ አላገኝም።

የኮንግረሱ አባላት ስደተኞች ፕሮግራሙን መቀየር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም በሚል ትኩረታቸውን በጤና እና በግብር ጉዳዮች ላይ አድርገዋል።