የታገቱ ማስታወሻ ደብተሮች፡ ክፍል 10

10) ታጣቂዎቹ ዜና በጥሞና ይከታተሉ ነበር

የእገታውን ማስታወሻ የቀድሞ ክፍሎችን ለማግኘት ፦

ብዙውን ጊዜ ቪድዮዎቹን ዜና ከተከታተሉ በኃላ ነበር የሚቀርጹት።

"ትንሽ ቆይተው ቢቢሲ ሃውዛን [በናይጄሪያ ቋንቋ] ያዳምጡ ጀመር። ልክ ሬድዮ አዳምጠው እነደጨረሱ አንድ በአንድ ጠሩን። አንዳንዶቻችንን እንድንበረከክ የተቀረነው ደግሞ እንድንቀመጥ አደረጉና የምናነበውን ሰጥተው መቅረጽ ጀመሩ። ከዚያ ከቁርአን አነበብን።''

ማስታወሻ ደብተሮቹን የጻፏቸው ልጃገረዶች የት ደረሱ?

ናኦሚ አዳሙና ሌሎች ሶስት ጸሐፊዎች ሮዳ ፒተር፣ ሳራቱ አዩባና ማርጋሬት ያማ ባለፈው ሚያዚያ ተፈትተዋል።

መስከረም ላይ መንግሥት በናይጄሪያ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ እንዲማሩ ተልከዋል።

አዳሙ ለቤተሰቦቿ ከሰባቱ አንዷ ስትሆን ማስታወሻዎቹን የጻፈችው ቤተሰቦቿን በማሰብ እንደሆነ ለጋዜጠኛ አዳዎቢ አጫውታታለች።

"ማስታወሻውን የጻፍኩት ወንድሞቼ፣ እህቶቼና ወላጆቼ እንዲያዩት ብዬ ነው" ትላለች

የምስሉ መግለጫ,

የናኦሚ እናት የማስታወሻ ደብተሩን ይዛ

የናኦሚ እናት ኮሎ ይባላሉ እሳቸው ማንበብ ባይችሉም ስለ ማስታወሻ ደብተሮቹ ይበልጥ ማወቅ እፈልጋለሁ ይላሉ።

ብዙውን የማስታወሻ መልዕክቶች ሳራ ሳሙኤል ብትጽፋቸውም ገና ስላልተመለሰች ጓደኛዋ ናኦሚ አዝናለች።

"እንደተጎዳሁ ይሰማኛል። እስካሁን እሷን ነው የማስበው። ''

ሳራ በታገቱ በሁለተኛው ዓመት ነበር የናይጄሪያ ወታደራዊ ኃይል ሲከባቸውና የቦኮ ሃራም መተዳደሪያ አቅርቦት ሲዘጋባቸው በፍርሃት ለማግባት የተስማማችው። በማግባቷም ምክንያት የነበሩበትን ካምፕ ከባለቤቷ ጋር ምግብ ወደሚገኝበት አካባቢና የተሻለ ሕይወት ወደሚመሩበት ጥላ ለመሄድ ተገደደች። ከመካከላቸው ትዳር ከመሰረቱት ውስጥ እስካሁን አንዳቸውም አልተለቀቁም።

የሳራ አባት አቶ ሳሙኤል ያጋ ለጋዜጠኛዋ የመጀመሪያ ልጁ መጽሃፏ ብዙም እንዳላስደነቀው አጫውቷታል።

"ሁሌ እንዳነበበች ነበር። አንዳንዴ መጽሐፍ እንደያዘች እንቅልፍ ይዟት ይሄድ ነበር'' በለዋል ።

በማስታወሻ ድበተሯ የመጨረሻው ገጽ ላይ የአምስት ወንድምና እህቶቿን ስሞች ጠቅሳለች በመጨረሻም " የአባቴ ስም ሳሙኤል ሲሆን እናቴ ደግሞ ርብቃ ትባላለች '' ብላ ጽፋለች።

መርሳት የማትፈልግ ይመስል ነበር።