ለካ እንቅልፍ እንዲህ ጠቃሚ ነገር ኖሯል?

የተኛች ህፃን ልጅ Image copyright MUNIR UZ ZAMAN

ስለ እንቅልፍ ጥቅምና ጉዳት ምን ያህል እናውቃለን? ከጤናችን፣ ከባህሪያችን እንዲሁም ከዕድሜያችን ጋር ስላለው ግንኙነትስ? እስቲ ስለእንቅልፍ እኒህን አስር ጠቃሚ ነጥቦች እንንገርዎ. . .

1. ለ8 ሰዓታት መተኛት

ብዙ ጊዜ በአንድ ቀን ቢያንስ ለስምንት ሰዓታት መተኛት እንዳለብን ሲነገር እንሰማለን። ግን ይህ መረጃ ከየት የመጣ ነው?

የእንቅልፍ እጥረት አለባቸው የምንላቸው ከስድስት ሰዓት ያነሰ እንቅልፍ የሚያገኙ ሰዎችን ሲሆን ከልክ በላይ የሆኑቱ ደግሞ ከዘጠኝ እስከ አስር ሰዓት የሚያንቀላፉ ሰዎች ናቸው።

ጥናቶች እንደሚያመለከቱት የእንቅልፍ እጥረት ያለባቸው ሰዎችም ሆኑ ከልክ በላይ እንቅልፍ የሚያገኙ ሁለቱም ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ ናቸው።

ታዳጊዎች እስከ 11 ሰዓታት ድረስ እንዲተኙ ሲመከር ጨቅላ ሕፃናት ግን በተለየ ሁኔታ እስከ 18 ሰዓታት ድረስ እንዲተኙ ይመከራል።

የደብሊን ስላሴ ኮሌጅ ፕሮፌሰር ሼን ኦማራ እንደሚናገሩት "እንዳንድ ጊዜ እንቅልፍ እጦት ለጤና መቃወስ ምክንያት ይሁን ወይስ ምልክት መለየት እጅግ አዳጋች ነው።"

የማይካደው ሐቅ ግን በተከታታይ የእንቅልፍ እጦት የሚያጋጥማቸው ሰዎች ለጤና መቃወስ እጅጉን የተጋለጡ ናቸው።

2. እንቅልፍ እጦት እና ሰውነታችን

እንቅልፍ እጦት ለጤና መታወክ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ መዛባቶች የሚያጋልጥ እንደሆነ በርካታ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

5 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የተሳተፉባቸው153 ጥናቶች እንዳመለከቱት በቂ እንቅልፍ የማያገኙ ሰዎች ለስኳር በሽታ፣ ደም ግፊት፣ ከልብ ጋር ለተያያዙ በሽታዎች እንዲሁም ከልክ ላለፈ ውፍረት ተጋላጭነታቸው የሰፋ ነው።

በጥናቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል ከሰባት ሰዓታት ያነሰ እንቅልፍ እንዲያገኙ የተደረጉ ሰዎች ለብርድ በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ብሎ ተገኝቷል።

ቁጣ ቁጣ ማለት፣ የአዕምሮ ችግር፣ እንዲሁም ከልክ በላይ ውፍረት ዋነኞቹ ችግሮች ሆነው ተገኝተዋል።

እንቅልፍ ያጠራቸው ሰዎች ሁኔታውን በመድሃኒት ለመመከት በሞከሩ ቁጥር ሰውነታቸው በሽታን ለመቋቋም ያለው አቅም እንደሚዳከምም ነው ጥናቶች የሚያስረዱት።

ከልክ በላይ እንቅልፍ መተኛትም የራሱ የሆኑ መዘዞች እንዳሉት አጥኚዎቹ ያሰምራሉ። ትልቁ የእንቅልፍ ማብዛት መዘዝ የማመዛዘን ችግር እንደሆነ ፕሮፌሰር ሼን ኦማራ ያስረግጣሉ።

Image copyright THONY BELIZAIRE

3. እንቅልፍ በደረጃ

እንቅልፍ ከ60 እስከ 100 ደቂቃዎች ርዝማኔ ያላቸው ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው ደረጃ በመተኛት እና አለመተኛት መካከል የሚገኝ ሰውነታችን ቀስ በቀስ ለቀቅ እያለ የሚመጣበት ክፍል ነው።

ሁለተኛው ክፍል ደግሞ በዝግመት ሙሉ በሙሉ ወደ እንቅልፍ የምንገባበት ነው። ሶስተኛው ደረጃ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ የምንተኛበት ክፍል ሲሆን ሰውነታችን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከሌሎች እንቅስቃሴዎች ውጭ የሚሆንበትና መነሳት የሚባል ነገር የማይታሰብበት ወቅት ነው።

ሰዎች በየዕለት ዕለት የእንቅልፍ ጊዜያቸው በእነዚህ ደረጃዎች ሥር የሚያልፉ ሲሆን የደረጃዎቹ መዛባት ለጤና መታወክ ሚና እንዳለውም ይነገራል።

4. የፈረቃ ሥራ እና እንቅልፍ

የፈረቃ ሥራ ብዙ ጊዜ ለበርካታ የጤና እክሎች ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይነገራል። አጥኚዎች እንደሚሉት ከልክ በታች እንቅልፍ የሚያገኙ የፈረቃ ሠራተኞች ከልክ ላለፈ ውፍረትና ለስኳር በሽታ ራሳቸውን አሳልፈው እየሰጡ ነው።

እንዲያም ሆኖ በፈረቃ ሥራ ሕይወታቸውን የሚመሩ ሰዎች ሙሉ በመሉ ለበሽታ የተጋለጡ ናቸው ማለት አይደለም። ለረዥም ጊዜ ያለምንም በሽታ መጠቃት የሚቆዩ እንዳሉም ጥናት ይዘግባል።

5. ከጊዜ ጊዜ የእንቅልፍ እጦት እያጠቃን ነው ይስ. . .?

እንቅልፍ እጦት እያስቸገረዎት ነው ተብለው ቢጠይቁ ምላሽዎ በእርግጥ ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም።

በ15 ሃገራት የተደረገው ጥናት ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ መረጃ ይዞ ብቅ ብሏል። ስድስት ሃገራት የእንቅልፍ ጊዜ ማጠር ሲስተዋልባቸው ሰባቱ ሃገራት ውስጥ ሰዎች የተሻለ እንቅልፍ እያገኙ ነው፤ የተቀሩት ሁለት ሃገራት ዜጎች ደግሞ የተመጣጠነ እንቅልፍ ያገኛሉ።

2ሺህ እንግሊዛውያን ወጣቶችን አካቶ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ሴቶች ከወንዶች በተለየ የእንቅልፍ እጦች ችግር አለባቸው። አልፎም ካፌይን እና አልኮልም የራሳቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ እንደሆነ ሳይረሳ።

በተለምዶ ምሽት ላይ የምናደርጋቸው እንደ ቴሌቪዥን መመልከት፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም እና ወጥቶ መዝናናት ያሉ እንቅስቃሴዎችም በቂ እንቅልፍ ላለማግኘት ትልቅ ሚና አላቸው።

6. ወደኋላ

"ከመቶ ዓመታት በፊት የነበረው ትውልድ በአንድ ቀን ውስጥ ሁለት የመኝታ ጊዜዎች ነበሩት" ሲሉ በቨርጂኒያ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ሮጀር ኤክሪች ያስረዳሉ።

በፕሮፌሰሩ ሃሳብ የማይስማሙ ሳይንቲስቶች ግን የኤሌክትሪክ ብርሃን በሌለበት ጊዜ የኖሩ አዳኝ ሰዎች በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነበር የሚተኙት ሲሉ ይከራከራሉ።

ይህም የሰው ልጅ ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ የእንቅልፍ ሥነ-ሥርዓቱ ተመሳሳይ እንደነበርና ብዙም እንዳልተለወጠ ያሳያል።

Image copyright Stanley Chou

7. ተንቃሳቃሽ ስልክ፣ እንቅልፍና ታዳጊዎች

የእንቅልፍ ባለሙያዎች እንደሚያስረግጡት በአስራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች በአንድ ቀን ቢያንስ የ10 ሰዓታት እንቅልፍ ማግኘት አለባቸው።

እውነታው ግን ቢያንስ ግማሽ የሚያህሉት እንኳ በዚህ መጠን እንቅልፍ እያገኙ አይደለም።

መኝታ ክፍሎች እንቅልፍ በሥርዓቱ የምናገኝባቸው ቦታዎች ሊሆኑ ሲገባ ተንቀሳቃሽ ስልክና ላፕቶፕ የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች እንቅልፍ እያሳጡን ነው። በተለይ ደግሞ በአስራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎችን።

8. የእንቅልፍ መዛባት ሕክምና

አሁን አሁን በርካታ ሰዎች በእንቅልፍ መዛባት ችግር ምክንያት እርዳታ በመሻት ወደ ሕክምና መስጫ ቦታዎች እየነጎዱ አንደሆነ ይነገራል።

ምክንያቱ በርካታ ሊሆን ቢችልም ዋነኛው ግን ከልክም በላይ ውፍረት እንደሆነ ነው አጥኚዎቹ አሁንም አጽንዖት ሰጥተው የሚናገሩት።

ዶክተሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ለታካሚዎች የእንቅልፍ መድሃኒቶችን ማዘዝ ማቆም ጀምረዋል። ከዛ ይልቅ ተከታታይ ሕክምና አዋጭ መላ ሆኖ ተገኝቷል።

ሆኖም አሁንም በርካቶቸ የእንቅልፍ መድሃኒቶችን ለችግሩ መከላከያ መላ አድርገው ይጠቀማሉ።

9. በሃገራት መካከል ያለው ልዩነትስ. . . ?

ኢንዱስትሪ በተስፋፋባቸው 20 ሃገራት የተካሄደ ጥናት እንደሚያትተው ከሞላ ጎደል በሃገራቱ መካከል ያለው የእንቅልፍ ዘይቤ ተመሳሳይነት አለው።

ጥናቱ እንደሚጠቁመው የሥራ ሰዓት፣ ትምህርት ቤት፣ እና የመዝናኛ ጊዜ ከተፈጥሯዊው የብርሃን ዑደት በበለጠ ሁኔታ የሰዎች የእንቅልፍ ስርዓት ላይ ተጽዕኖ አለው።

የኤሌክትሪክ አቅርቦት በሌለባቸው የታንዛኒያ፣ ናሚቢያ እና ቦሊቪያ አካባቢዎች የተደረገ ሌላ ጥናት ደግሞ ሰዎች በአማካይ 7.7 ሰዓት እንቅልፍ ያገኛሉ።

ይህም ኢንዱስትሪ ከተስፋፋባቸው ሃገራት ብዙም ልዩነት ያለው አይደለም።

Image copyright Dan Kitwood

10. የምሽት ወይስ የጠዋት ሰው ኖት. . . ?

በጥዋት ነቅተው ቀናቸውን የሚጀምሩ ሰዎች መኖራቸውን ያህል ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ በዓይናቸው ሳይዞር የሚነጋ ሰዎች ደግሞ ያጋጥሙናል።

መብራት እንቅልፍ ሳይተኙ ሌሊቱን ለሚያሳልፉ ሰዎች ትልቅ እፎይታን ፈጥሯል።

ለጥናት ታስቦ መብራት ወደሌለበት ሥፍራ የተወሰዱ ሰዎች በ48 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ቀድመው ከሚተኙበት ጊዜ በሁለት ሰዓታት አስቀድመው ወደ መኝታቸው አምርተዋል።

ጊዜ በገፋ ቁጥርም ሰዎች ፀሓይ ስታዘቀዝዝቅ ወደ መኝታቸው መሄድ ተያያዙት።

ዋናው ነጥብ ሰውነታችን የሚከተለውን ተፈጥራዊ ሂደት በሰው ሰራሽ አምፖል መመከቱ የሚመከር አይደለም ሲሉ አጥኚዎቹ ያሰምራሉ።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ