የትራምፕ ትዊተር ገጽ በኩባንያው ሠራተኛ ተዘጋ

የትዊተር መልዕክት

የፎቶው ባለመብት, Twitter

የምስሉ መግለጫ,

የትራምፕን የትዊተር ገጽ ተዘግቶ በቆየባቸው ደቂቃዎች ተጠቃሚዎች ማየት የቻሉት "Sorry, that page doesn't exist!" (ይቅርታ ገጹ አልተገኘም) የሚለውን መልዕክት ብቻ ነበር።

የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የትዊተር ገጽ ዕለተ ሃሙስ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ከተዘጋ በኋላ እንዲከፈት መደረጉን ትዊተር አስታውቋል።

ትዊተር ማንነቱን ያልገለፀው ሠራተኛ የዶናልድ ትራምፕን የትዊተር ገጽ @realdonaldtrump እንዲዘጋ ወይም ከጥቅም ውጭ እንዲሆን በማድረጉ ሠራተኛውም በኩባንያው የመጨረሻው ቀን ነው ብለዋል።

የትራምፕ ትዊተር ገጽ ለ11 ደቂቃዎች ያህል ነው ተዘግቶ የቆየው።

ከ41 ሚሊየን በላይ ተከታዮች ያላቸው ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2009 ጀምሮ ከ36,000 በላይ ሃሳቦችን ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

'የራተኛው የመጨረሻ ቀን'

ትዊተር "ጉዳዩን እያጣራሁ ነው። ይህ ዓይነት ክስተት በድጋሚ እንዳይከሰት የተለያዩ እርምጃዎችን እንወስዳለን" ሲል አስታውቋል።

''ባደረግነው ማጣራት የትራምፕ ገጽ የተዘጋው በደንበኞች ድጋፍ አገልግሎት ሰጪ ሠራተኛችን መሆኑን ደርሰንበታል። ይህም ለሠራተኛው የመጨረሻው ቀን ነው'' ብሏል ትዊተር።

የፎቶው ባለመብት, Twitter

ዶናልድ ትራምፕ የትዊተር ገጻቸው እንደገና እንዲሠራ ከተደረገ በኋላ የመጀመሪያው ትዊታቸው ስለ ሪፓፕሊካኖች የግብር ቅነሳ በተመለከተ ነበር።

ትራምፕ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት እና የፕሬዝዳንትነት ሥልጣንን ከተረከቡ በኋላ ትዊተርን አብዝቶ በመጠቀም ፖሊሲዎቻችውን ከማስተዋወቅ አልፎ ለፖለቲካ ተፎካካሪዎቻቸው ምላሽም ይሰጡበታል።