በሚመጣው እሁድ ሲቲ ከአርሴናል፤ ቼልሲ ከዩናይትድ ማን ድል ይቀናው ይሆን?

ላውሮ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

ማንችስተር ዩናይትድ ባለፈው ሳምንት መርሃ-ግብር ቶተንሃምን አስተናግዶ ማሸነፍ ችሏል፤ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞም ይገኛል።

በዚህ ሳምንት ደግሞ ወደ አምናው የዋንጫ አሸናፊ ቼልሲ በመጓዝ ፍልሚያውን ያደርጋል። ዩናይትድ ከዚህ ጨዋታ የተሻለ ነጥብ ያገኝ ይሆን?

የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ማርክ ላውረንሰን በስታንፎርድ ብሪጅ የሚደረገው ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት እንደሚያልቅ ይገምታል።

እነሆ የዚህንና የሌሎች ቀሪ ጨዋታዎችን ግምት ከላውሮ።

ቅዳሜ

ስቶክ ከሌይስተር

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

ስቶክ ሲቲዎች ባለፈው ቅዳሜ ዋትፎርድን 1-0 በማሸነፍ ከሜዳቸው ውጭ ነጥብ ይዘው መመለስ ችለዋል። ስቶኮች ውጤቱን እጅጉን ይፈልጉትም ነበር።

አቻ ውጤት ከሌይስተር ይልቅ ስቶክ ሲቲን ሊያስከፋ እንደሚችል አስባለሁ። አቻ መለያየት ለሌይስተር ያለመሸነፍ ጉዞው እንደሚያሳምር ባውቅም ለስቶክ ግን አቻ ውጤት ምንም ትርጉም የለውም።

የላውሮ ግምት፡ 1 - 0

ሃደርስፊልድ ከዌስትብሮም

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

ለሃደርስፊልዶች ሜዳቸው ላይ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች እጅግ ወሳኞች ናቸው። ማንቸስተርን ካሸነፉ በኋላ ከሊቨርፑል ጋር ያሳዩት አቋም እጀግ ደካማ ነበር።

አሁን ከዌስትብሮም ጋር በሚኖራቸው ፍልሚያ ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደሚሯሯጡም አስባለሁ።

ነገር ግን ዌስትብሮም ወደ ሃደርስፊልድ ሜዳ ሄዶ ያሸንፋል ነው የኔ ግምት።

የላውሮ ግምት፡ 0 - 2

ኒውካስል ከቦርንማውዝ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

ኒውካስል ባለፈው ከበርንሌይ ጋር የነበረውን ጨዋታ ተመልክቻለሁ፤ አሪፍ ኳስ ይጫወታሉ። ነገር ግን ኳስ ወደ ጎል መቀየር ላይ ችግር አስተውዬባቸዋልሁ።

ቦርንማውዞች በዚህ ወር የተሻለ ነገር ለማምጣት ቆርጠው የተነሱ ይመስላል። መካከለኛ ደረጃ ላይ ላሉ ቡድኖች አቻ ውጤት ጥሩ እንደሆነ እገምታለሁ።

የላውሮ ግምት፡ 1 - 1

ሳውዝሃምፕተን ከበርንሌይ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

የሳውዝሃምፕተኑ አሰልጣኝ ሞሪሲዮ ፔሌግሪኖ ከራፋዬል ቤኒቴዝ ጋር ሊቨርፑልን አሰልጥነዋል። እስካሁን ቡድናቸው በ10 ጨዋታ 9 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል። ከዚህ በላይ እንዲያስቆጥሩ የሚያስችሏቸው አጥቂዎች እንዳሏቸውም አውቃለሁ።

በዚህ ጨዋታም የተሻለ ነጥብ እንደሚያስቆጥሩ እገምታለሁ።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 1

ስዋንሲ ከብራይተን

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

ስዋንሲ ቅርፁ ምንም የማይገባ ቡድን ነው፤ ምክንያቱም በአንድ ጨዋታ በጣም የወረደ አቋም ያሳያሉ በሚቀጥለው ደግሞ በጣም አስገራሚ ይሆናሉ።

ብራይተን እያሳየው ባለው አቋምም እጅግ ተደስቻለሁ። ጥሩ ባልሆኑበት ጨዋታ እንኳ ነጥብ ይዘው ይወጣሉ።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 1

ዌስትሃም ከሊቨርፑል

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

ዌስትሃሞች ጥሩ አቋም ያላቸው ተጨዋቾችን ቢይዙም የመከላከል ኃይላቸው ግን ደካማ ነው። እዚህ ላይ ትልቅ ትኩረት ያሻቸዋል።

የስሌቫን ቢሊች ቡድንን አይተው ቡድኑ የሊጉ ሰንጠረዥ ወገብ አካባቢ ቦታ ላይ ተደላድሎ መቀመጥ ነበረበት ቢሉ ትክክል ነዎት።

የላውሮ ግምት፡ 0 - 2

ዕለተ እሁድ

ቶተንሃም ከክሪስታል ፓላስ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

ረቡዕ ዕለት ከማድሪድ ጋር ከነበራቸው ጨዋታ በኋላ ቶተንሃሞች በጣም አስገራሚ መንፈስ ላይ እንደሚገኙ አስባለሁ። ፖቸቲኖ አሁን ላይ እጅግ ተዘጋጅቶ እንደሚገኝም አምናለሁ።

ፓላሶች አሁንም ወራጅ ቀጣና ላይ ሊገኙ ይችላሉ ነገር ግን አቋማቸው ከሮይ ሆድሰን በኋላ እጅጉን ተሻሽሏል፤ ቼልሲንም አሸንፈዋል። ከኒውካስል ውጤት ማግኘት ነበረባቸው፤ ባለፈውም አቻ ውጤት አግኝተዋል።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 0

ማንችስተር ሲቲ ከአርሴናል

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

አሁን ላይ ሲቲን የሚያቆም ያለ አይሰማኝም፤ ነገር ግን ይቻላል። ማግኘት ከነበረባቸው 30 ነጥብ 28ቱን በመሰብሰብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጠዋል።

አርሰን ቬንገር ብዙ ጊዜ ከሃያል ክለቦች ጋር ሲጫወቱ "ኳስ እንጫወታለን" ሲሉ ይደመጣል። ከሲቲ ጋር በሚኖራቸው ጨዋታ አጥቅተው ይጫወታሉ የሚል እምነት የለኝም።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ቬንገር ወደ ሲቲ ተጉዘው 2-0 አሸንፈው እንደመጡ አስታውሳለሁ። ነገር ግን አሁን ላይ ያንን ማድረግ ይችላሉ ብዬ አላምንም።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 0

ቼልሲ ከማንችስተር ዩናይትድ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

የሞሪንሆው ማንችስተር ዩናይትድ ከሃያላኑ ጋር ከሜዳው ውጭ ሲጫወት ነጠብ ይዞ ይመጣል። ይህንንም ከሊቨርፑል ጋር በነበረው ፍልሚያ ተመልክተናል።

ቼልሲ ሜዳ ላይም ተመሳሳይ ነገር እንደምናይ እገምታለሁ። የዩናይትድ ተጫዋቾች ኳስ ወደ ቅጥራቸው እንዳይዘልቅ ለማድረግ እንድሚዋደቁም አስባለሁ።

የላውሮ ግምት፡ 1 - 1

ኤቨርተን ከዋትፎርድ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

የኤቨርተኑን ጊዜያዊ አሰልጣኝ ዴቪድ አንስዎርዝን በደንብ አውቀዋለሁ። የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ይሸነፋል ብዬም አልገምትም። በተመሳሳይ ተጨዋቾች ከኮማን የተሻለ ነገር ለማሳየት እየጣረ እንደሆነም አውቃለሁ።

የዋትፎርዶች አጀማመር ጥሩ የነበረ ቢሆንም ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። አሁን ላይ ስላሉበት አቋም እርግጠኛ ሆኖ መናገር ያዳግታል።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 0