የሴቶች እኩልነት በመጪዎቹ 100 ዓመታትም አይረጋገጥም- የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም

የሴቶችን የወንዶች ሚዛን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለውን የጾታ ልዩነት ለማጥበብ መቶ ዓመታት እንደሚፈጅ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም አስታውቋል።

የፎረሙ መረጃ ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ በየዓመቱ እየተባባሰ የመጣውን የጾታ ልዩነት የሚያሳይ ነው።

ሪፖርቱ 144 ሃገራትን በኢኮኖሚ እድል፣ በትምህርት፣ በፖለቲካ ተሳትፎና በጤና ደረጃ አውጥቶላቸዋል።

ሴቶች ወንዶች ከሚያገኙት ዕድልና ውጤት 68%ውን ብቻ እንደሚያገኙ ይገልጻል፤ ባለፈው ዓመት ግን 68.3% ነበር።

እናም ባለፈው ዓመት ክፍቱን ለመሙላት ያስቀመጠውን የ83 ዓመታት ጊዜ ከፍ በማድረግ 100 ዓመታት አድርሶታል።

በእርግጥ በጤናና ትምህርት ክፍተቱ እየጠበበ ቢሆንም በኢኮኖሚና በፖለቲካ ተሳትፎ ግን በጣም ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ጥናቱ አረጋግጧል።

እናም ሴቶች በሥራ ቦታቸው ከወንዶች እኩል እንዲወከሉ ተጨማሪ 217 ዓመታትን መጠበቅ ግድ እንደሚል ነው የገለጸው።

የኖርዲክ ሃገራት በጾታ እኩልነት የተሻለ ደረጃ ላይ ሲገኙ በአይስላንድ ያለው ክፍተት የ12% ብቻ ነው።

ኖርዌይ፣ ፊንላንድና ስዊዲንም ከመጀመሪያዎቹ 5 ሃገራት ተርታ ተመድበዋል።

በፓርላማ ከአምስት ወንበሮች ሶስቱ በሴቶች የሚወከሉባት አፍሪካዊቷ ሩዋንዳ በ18 በመቶ አራተኛ ደረጃን ይዛለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የመን በሴቶች የፖለቲካና የትምህርት ተሳትፎ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች

በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪካ የሚገኙ ሃገራት ግን ሁኔታው የተባባሰባቸው ናቸው።

በጦርነት እየታመሰች ያለችው የመን በ52 በመቶ ክፍተት የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች።

ሪፖርቱ ሴቶች ከወንዶች ያነሰ ደሞዝ እንደሚያገኙና ግፋም ሲልም ክፍያ በሌላቸውና በትርፍ ጊዜ ሥራዎች እንደሚሰማሩ ይዘረዝራል።

ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት ደግሞ በሴቶች ጤና ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን ይጠቅሳል።

ሴት ሰራተኞችን በማሰማራት በመጀመሪያዎቹ 20 ደረጃዎች 9ኙ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት የተያዙ ናቸው።