"ወገን የሌለው ሰው አቅሙ ጉልበቱ ላይ ነው"

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
"በዓለም አቀፍ ውድድሮች በመሳተፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ነው ዓላማዬ"

መድኃኔ ኃይለ ዘወትር ማልዶ እየተነሳ በመቐለ ጮምዓ ተራራ ላይ የሩጫ ልምምድ ያደርጋል።

ይህ የልቡም ፍላጎት፣ የድህነትም መውጫ በር እንደሆነ ቢያውቅም ከልምምዱ ሲመለስ ደግሞ ሌላ የህይወት ሩጫ ይጠብቀዋል።

ልክ እንደተለመሰ የሊስትሮ እቃውን ይዞ በመቐለ ከተማ አጼ ዮሐንስ ሆቴል አካባቢ አንገቱን ደፍቶ ጫማ ይጠርጋል።

መድኃኔ በአስመራ ከተማ ተውልዶ የ13 ዓመት ልጅ እያለ ነበር ከወላጆቹ ጋር ወደ መቐለ የመጣው።

በአስመራ እስከ 5ኛ ክፍል ፣ በመቐለ ደግሞ እሰከ 12 ክፍል ተምሮ በ2005 የሁለተኛ ደረጅ ትምህርቱን አጠናቋል።

10ኛ ክፍል ሲደርስ ነበር ጫማ መጥረግና መስፋት የጀመረው ። የኑሮ ትግሉ ቢያሸንፈው ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዶ ነበር።

እርሱ ቤተሰቡን ጫማ በመጥረግ ሲደግፍ እናቱ ደግሞ በመቐለ መሃል ገበያ ቅመማ ቅመሞችን ዘርግተው ይሸጣሉ።

ወላጅ አባቱም በቀዳማይ ወያነ አስተዳደር በዘበኝነት ተቀጥረው እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ።

እናም ቤተሰቡ በእንደዚህ ዓይነት ኑሮ የሚገኘው ወጣት ከድህነት ለማምለጥ እዚህም እዚያም ይሮጣል።

ሩጫው ቢክብድም መድኃኔ ግን አልደከመም፤ ጫማ እየሰፋ እስከ 12 ኛ ክፍል ተማረ ።

በየቀኑ ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ እየጠረገም፣ እየሰፋም እስከ 40 እና 50 ብር ገቢ ያገኛል።

"ሳምንት ሙሉ ስለምሮጥ ገቢዬ ትንሽ ነው፤ በእሁድ ነው የማካክሰው፤ እሁድ ስለማልሮጥ ቀኑን ሙሉ እሰራለሁ ፤ ኑሮ እንደሚከብደኝማ ምን ጥያቄ አለው?" ይላል።

በወር 700 ብር በሚከፍልበት የኪራይ ቤት ዝወትር ምግቡን ያበስላል፤ ልብሱን ያጥባል፤ እንደገና ወደ ጫማ መስፋቱ (መጥረጉ) ይገባል።

አንድ ቀን በሩጫ እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ሆኖ ያወራል።

"ከልብ ካመንክበት ከምንም ተነስተህ ወደ ድል እንደሚደረስ አምናለሁ። ወገን የሌለው ሰው ወገኑ ጉልበቱ ነው"

ቤተሰቦቹ ግን ሩጫ የሚባል ነገር አይዋጥላቸውም። "የሚሮጠው የሃብታም ልጅ ነው። አንተ ምን በልተህ ትሮጣለህ? ይቅርብህ " ይሉታል።

እርሱ ግን ቀነኒሳ ሲሮጥ ካየ በኋላ ልዩ የሩጫ ፍቅር ስላደረበት የነርሱ ሃሳብ አልተዋጠለትም።

በቀነኒሳ አሯሯጥ በጣም ይማረካል። ማሸነፍ የሚፈልገው ግን በራሱ መላ ነው።

ልምምድ የሚሰራበት ማሊያ አዲስ አባባ ያለው አጎቱ ሲገዛለት ሁኔታውን የሚያውቁ ደንበኞቹም ያግዙታል።

በገንዘብም ሆነ በዓይነት የሚገለፅ ሌላ እርዳታ ግን እስካሁን አላገኘም።

ለዚህ ነው መድኃኔ በርትቶ በመስራት መቐለን መወከል፣ ከዚያም በክለቦች የመታቀፍ እድሉን የማስፋት ህልም ያለው።

ግን ይህ መኞቱ በሕይወት ሩጫ ምክንያት እንዳይደበዘዝ ስጋት አለው።

"ሩጫ ላይ በፅናት እየሰራሁ ስለሆነ ለውጥ አምጥቻለሁ። ችግሩ ከሮጥኩ በኋላ እረፍት የለኝም። ጉልበቴ ከግዜ ወደጊዜ እቀነሰ መጥቷል" ይላል።

ግን መቼም ቢሆን ለህልሙ መሳካት ይታትራል።