የቴክሳስ ተኳሽ 26 ሰዎችን መግደሉ ተሰማ

shooting in Sutherland Springs, Texas

የፎቶው ባለመብት, KSAT 12 / Reuters

ዕለተ እሁድ ረፋድ 5፡30 አካባቢ በቴክሳስ ግዛት ሱዘርላንድ ስፕሪንግ አካባቢ ቤተክርስትያን ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ አንድ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ 26 ሰዎችን ሲገደል በርካቶችን ማቁሰሉ ተሰምቷል።

የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ግሬግ አቦት 26 ሰዎች መሞታቸውን ገልጠው ግድያው በቴክሳስ ታሪክ እጅግ አሰቃቂው ነው ሲሉ ተሰምተዋል።

የቴክሳስ ሕዝብ ደህንነት ኃላፊ ፍሪማን ማርቲን በበኩላቸው ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 72 የሚደርስ ሰዎች የግድያው ሰለባ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የግዛቲቱ ባለስልጣናት ቢያንስ 20 ሰዎች መቆሰላቸውንና ለእርዳታ ወደ ሕክምና ጣቢያ መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

ተዃሹ በሃያዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኝ ነጭ ግለሰብ እንደሆነ ያስታወቁት ማርቲን ጥቁር ለብሶና የጦር መሣሪያ ታጥቆ ወደ ሥፍራው በመምጣት ተኩስ እንደከፈተ ተናግረዋል።

ተኳሹ ወደ ሰዎች መተኮስ ሲጀምር የተመለከተ ግለሰብ የራሱን መሣሪያ አውጥቶ መተኮስ እንደጀመረና ገዳዩም በመኪና ለማምለጥ ሲሞክር ከተሽከርካሪ ጋር ተጋጭቶ ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ ተናግሯል።

ተኳሹ ዴቪን ኬሊ የተባለ የ26 ዓመት ግለሰብ እንደሆነ የአሜሪካ ሚድያዎች ቢዘግቡም ፖሊስ ግን የተኳሹን ሙሉ ማንነት ገና አለማጣራቱን ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የቤተክርስትያኗ ፓስተር ፍራንክ ፖሜሮይ ኤቢሲ ለተባለው ጣቢያ "ውቧን የ14 ዓመት ሴት ልጄን ጨምሮ ገዳዩ የብዙ ሰው ሕይወት አጥፍቷል" ሲሉ ተናግረዋል።

ፖሊስ የተጎጂዎችን ማንነት እስካሁን ይፋ ያላደረገ ቢሆንም የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነ ግን አረጋግጧል።

23 ግለሰቦች ቤተክርስትያኗ ውስጥ ሞተው የተገኙ ሲሆን 2 ሰዎች ደግሞ ውጭ ላይ ተተኩሶባቸው ሕይወታቸው ሲያልፍ አንድ ግለሰብ ወደ ሕክምና መስጫ በመሄድ ላይ ሳለ እንደሞተ ታውቋል።

የአሜሪካ ፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ቦታው ምርመራ ላይ እንደሆነ አስታውቆ ግለሰቡ ድርጊቱን የፈፀመበት ምክንያት ግን እስካሁን ግልፅ እንዳልሆነ አሳውቋል።

በአህጉረ እስያ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት ትራምፕ "የክፋት ድርጊት" በማለት ሁኔታውን ሲኮንኑ "ምንም ሃዘን ላይ ብንሆን በጋራ ጠንክረን እንቆማለን" በማለት አክለዋል።

ከአንድ ወር ገደማ በፊት አንድ ግለሰብ በላስ ቬጋስ የሙዚቃ ድግስ በመከታተል በነበሩ ሰዎች ላይ በከፈተው ተኩስ 58 ሰዎችን መግደሉ የሚታወስ ነው።