የእንግሊዝ የፕሪሚዬር ሊግ የሳምንቱ ምርጥ 11

ማንችስተር ሲቲ የማሸነፍ ጉዞውን በመቀጠል በስምንት ነጥቦች ልዩነት ሊጉን መምራቱን ተያይዞታል።

ሆዜ ሞሪንሆ ወደ ስታንፎርድ ብሪጅ ተመልሰው ሽንፈት ቀምሰው ተመልሰዋል። ሊቨርፑል በበኩሉ ዌስትሃምን 4-1 ረምርሞታል። አቬርተን በሚገርም ብቃት 2-0 ከመመራት ተነስቶ 3-2 መርታት ችሏል።

ሃደርስፊልድ፣ ቦርንማውዝ፣ በርንሌይና ብራይተን ተጋጣሚዎቻቸውን 1-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፉ ስቶክ ከሌይስተር 2 አቻ ተለያይቷል።

ከእነዚህ ሁላ ፍልሚያዎች በኋላ በጋርዝ ክሩክስ የሳምንቱ ምርጥ 11 ውስጥ የተካተቱት እነማን ይሆኑ?

ግብ ጠባቂ- ኒክ ፖፕ (በርንሌይ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኒክ ፖፕ በዚህ ውድድር ዘመን ከማንኛውም ግብ ጠባቂ በላይ ኳስ በማዳን ምርጥ መሆኑን አሳይቷል።

የሳውዝሃምፐተኑ ሶፍያን ቦፋል የላካትን ኳስ ኒክ ፖፕ ያዳነበት መንገድ ጥሩ ነበር። ነገር ግን እጅግ ያስገረመኝ የናታን ሬድሞንድን ኳስ ያዳነበት መንገድ ነው።

የበርንሌዩ ዋና ግብ ጠባቂ ቶም ሂተን ከተጎዳ በኋላ ተክቶ የገባው ፖፕ ምርጥ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል።

ተከላካይ - ስቲቭ ኩክ (ቦርንማውዝ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስቲቭ ኩክ ጎል ባስቆጠረባቸው ስድስት የሊግ ጨዋታዎች በሙሉ ቦርንማውዝ ማሸነፍ ችሏል።

ቦርንማውዝ ከኒውካስል ያደረገው ጨዋታ ዜሮ ለዜሮ መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም በባከነ ደቂቃ ስቲቭ ኩክ ከማዕዘን የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለቡድኑ ሶስት ነጥብ ማስግኘት ችሏል።

ተከላካይ - ሼን ዳፊ (ብራይተን)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሼን ዳፊ በያዝነው የውድድር ዘመን ከማንኛውም ተከላካይ በተሻለ በጭንቅላቱ ኳስ በማውጣት ሪከርድ ይዟል።

ብራይተን ከሲቲ ጋር የነበራቸውን የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ስመለከት በሊጉ ሃያ ነጥብ እንኳ ያመጣሉ የሚል እምነት አልነበረኝም። አሁን ግን 15 ነጥብ ይዘው ስመለከት ተሳስቼ እንደነበር አምኛለሁ።

ክሪስ ሂዩተን በተጫዋቾቻው ላይ ያሳደሩት እምነት እጅግ እየላቀ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ። ሼን ዳፊም በአሰልጣኙ እምነት ከተጣለባቸው መካከል ቁንጮው እንደሚሆን እምነቴ ነው።

ተከላካይ - ሌዊስ ዳንክ (ብራይተን)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሌዊስ ዳንክ በዚህ ዓመት እያሳየ ያለው የመከላከል ብቃት እጅግ አስገራሚ ነው።

ከስዋንሲ አጥቂዎች የሚላኩ ኳሶችን በመመከት ብራይተን ድል ተቀዳጅቶ እንዲወጣም የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል።

አማካይ - ኬቪን ደብሩይን (ማንቸስተር ሲቲ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለሲቲ መጫወት ከጀመረበት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ኬቪን ደብሩይን ከማንኛውም ተጫዋቻ በተሻለ ኳስ ለጎል አመቻችቶ አቀብሏል።

ድብሩይን የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ምርጫዬ ውስጥ መግባት ችሏል። ለጎል የሚሆኑ ኳሶች አመቻችቶ የሚያቀብልበት መንገድ በጣም አስገራሚ ነው። ነገር ግን ጎል ማስቆጠር መቻሉ በራሱ ሌላ ድንቅ ብቃት ነው።

ሲቲ አርሴናል ላይ ያስቆጠራት ሁለተኛ ጎል ከጨዋታ ውጭ እንደሆነች ባምንም መድፈኞቹ ከፍልሚያው ነጥብ እንደማያገኙ ግን አውቅ ነበር። ሲቲ ድንቅ ብቃት እያሳየ ያለ ሲሆን ለዚህም የደብሩይን አስተዋፅኦ ከሚገለጸው በላይ ነው።

አማካይ - ጎሎ ካንቴ (ቼልሲ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቼልሲ በዩናይትድ ጎል ሳይቆጠርበት ለመውጣቱ ትልቁ ምክንያት የኒጎሎ ካንቴ ብቃት ምርጥ መሆኑ ነው።

ቲብዋት ኮርትዋ ያዳናቸው የተወሰኑ ኳሶች እንዳሉ ሆነው የካንቴ መከላከል ግን ዩናይትድን አንድ ነጥብ እንኳ እንዳያገኝ አድርጎታል።

ከጉዳት ከተመለሰ ወዲህም ለቡድኑ መጠናከር የተሻለ አስተዋፅኦ አድርጓል።

አማካይ - ኤደን ሃዛርድ (ቼልሲ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከባለፈው ዓመት የውድድር ዘመን ጀምሮ ሃዛርድ ከማንኛውም የቼልሲ ተጫዋች በተሻለ ቡድኑ በሚያስቆጥራቸው ጎሎች ውስጥ እግሩ አለበት።

በኮንቴና በሞሪንሆ መካከል የነበረው ግድየለሽ ሰላምታ በሁለቱ አሰልጣኞችና ቡድኖች መካከል ያለውን ፉክክር የሚያሳይ ነበር። በዚህ ሁኔታ የቼልሲ ተጫዋቾች ለዩናይትድ ነጥብ አሳልፈው እንደማይሰጡም እሙን ነበር።

በዚህ ፍልሚያ ሃዛርድ በእያንዳንዱ ኳስ የነበረው ጥንቃቄ ለቼልሲ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣት የቡኩሉን ተጫውቷል።

አመካይ - ራጂቭ ቫን ላ ፓራ (ሃደርስፊልድ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ላ ፓራ ለተከታታይ 23 ጨዋታዎች ለሃደርስፊልድ ተስለፎ በስተመጨረሻም ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ላ ፓራ ዌስትብሮም ላይ ያስቆጠራት ጎል እጅግ ማራኪ ከመሆንዋ የተነሳ በተደጋጋሚ ብመለከታት አይሰለቸኝም። ቤን ፎስተር ኳሷን ቆሞ ከመመልከት ውጭ ምንም አማራጭ አልነበረውም።

የሃደርስፊልዱ ግብ ጠባቂ በጨዋታው የመጨረሻው ደቂቃዎች ላይ ያሳየው አቋምም የሚናቅ አልነበረም።

አጥቂ - ሞሓመድ ሳላህ (ሊቨርፑል)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሞሓመድ ሳላህ በመጀመሪያዎቹ 11 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ በዘጠኝ ጎሎች ውስጥ እግሩን ማስገባት ችሏል።

ሊቨርፑል ከዌስትሃም የነበረው ጨዋታ ፍልሚያ ሳይሆን ውድድር ነበር የሚመስለው። ምክንያቱም ሊቨርፑል ምርጥ ሆኖ ሳይሆን ዌስትሃም ደካማ ስለሆነ ነበር ሶስት ነጥብ ማግኘት የቻለው።

ግብጻዊው አጥቂ እጅግ ፈጣንና ማራኪ ጨዋታ ማሳየት ችሏል። በስድስት ጨዋታዎችም አምስት ጎሎች ማስቆጠርም ችሏል።

አጥቂ - አልቫሮ ሞራታ (ቼልሲ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አልቫሮ ሞራታ ከባለፈው ዓመት የውድድር ዘመን ጀምሮ በተጫወተባቸው ሊጎች አስር ኳሶችን በግንባሩ ማስቆጠር ችሏል። ይህም በአውሮፓ ምርጡ ያደርገዋል።

ሞራት በግንባሩ ካስቆጠራት ምርጥ ጎል ባለፈ ግን እኔን ያስገረመኝ ከሃዛርድ ጋር የነበረው አስገራሚ ጥምረት ነበር።

ኮንቴ ተጫዋቹን የሚፈልጉት ከሆነ ጸባዩ እንዴትም ይሁን እንዴት ሊንከባከቡት ይገባልም ባይ ነኝ።

አጥቂ - ሪያድ ማህሬዝ (ሌይስተር)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፉት አራት የሌይስተር ጨዋታዎች ማህሬዝ ሁለት ጎል ሲያስቆጥር ሁለት ኳሶች ለጎል አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ለሁለት ተከታታይ ሳምንታትም በምርጥ 11 ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ መግባት ችሏል።

ከሌይስተር ጋር እንደነበረው ፍልሚያ ሁሉ ማህሬዝ ስቶክ ላይ ጫና ማሳደር ችሏል።