ወባን በትንፋሽ መለየት የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ተስፋ እንዳለው ተገለፀ

malaria breath test

ትንፋሽን ለመሣሪያው በመስጠት ብቻ ወባ መኖር አለመኖሩን መለየት የሚያስችለው ቴክኖሎጂ በአፍሪካ ሙከራ እንደተደረገበት ታውቋል።

ሙከራው ወባ በሚታይባቸው አካባቢዎች በሚኖሩ ሕፃናት ላይ ተሞክሮ ተስፋ ሰጭ ሆኖ ቢገኝም መሻሻል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ተገልጿል።

መሣሪያው የወባ አሰራጭ የሆነችው ትንኝ የሚስባትን ተፈጥሯዊ ሽታ ተክትሎ ነው በሽታውን የሚያጣራው።

ሳይንቲስቶቹ እንደሚናገሩት የወባ ትንኝን የሚስበው የተፈጥሮ ሽታ የወባ በሽታ ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚታይ ነው።

ምንም እንኳ መሣሪያው መሻሻል ቢኖርበትም በጣም ርካሽ የሆነ የወባ መመርመሪያ መሣሪያ እንደሚሆን ግን እየተነገረ ይገኛል።

ልዩ ሽታ

ሙከራ ላይ ያለው መሣሪያ በዋናነት ስድስት ለየት ያሉ ሽታዎችን የሚለይ ሲሆን ይህም በበሽታው ተጠቂ የሆነን ሰው እንዲለይ ያስችላል።

ተመራማሪዎች ይህንን በመጠቀም ከማላዊ በሽታው ያለባቸውን እና ነፃ የሆኑ 35 ሕፃናትን በመመልመል ሙከራ አድርገዋል።

ከተመረመሩት ሕፃናት መከካል ሃያ ዘጠኙ በትክክል ውጤታቸው ታውቋል። ይህም ማለት መሣሪያው 83 በመቶ ሙከራውን በድል ማጠናቀቅ ችሏል።

መሣሪያውን አሻሽለው በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ውደ ሥራ እንደሚያስገቡ በማሰብ፤ውጤቱ አኩሪ ባይሆንም እጅግ ተስፋ ሰጭ ነው ይላሉ ተመራማሪዎቹ

ፈጣንና ቀላል የወባ መመርመሪያ መሣሪያዎች ገበያው ላይ ቢኖሩም አሁንም ውስንነት አላቸው ሲሉ ተመራማሪዎቹ ይከራከራሉ ።

ደም ምርመራ ሕክምና ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች ውድ እና አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ይህኛው መሣሪያ ግን ደም መውሰድ ሳይጠይቅ በቀላሉ ውጤት ማሳወቅ ይችላል።