የቴክሳሱ ገዳይ በ2012 ከአዕምሮ ሆስፒታል አምልጧል

የቴክሳሱ ገዳይ በ2012 ከአዕምሮ ሆስፒታል አምልጧል Image copyright Getty Images

ከአምስት ቀናት በፊት ዴቪን ኬሊ ለራሱና በቅርቡ ላሉ ሰዎች አደጋ እንደሆነ የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎች ማሳወቃቸውን የፖሊስ ሪፖርት አሳይቷል።

ኬሊ በቀድሞ ሚስቱና የእንጀራ ልጁ ላይ ባደረሰው የቤት ውስጥ ጥቃት ነው ወደ አዕምሮ ሕክምና መስጫ ጣቢያ የተላከው።

ከዛም አልፎ ይሠራበት የነበረውን የአሜሪካ አየር ኃይል ላይ ጥቃት ለማድረስ ይዝት እንደነበረም ታውቋል።

ባለስልጣናት እንደሚሉት ኬሊ በእንደዚህ ሁኔታ የጦር መሣሪያ የመታጠቅ መብቱን ሙሉ በሙሉ መነጠቅ ነበረበት።

ኤል ፓሶ የተባለው ገዳዩ ይኖርበት የነበረ አካባቢ ፖሊሶች ሰኔ 2012 ላይ ነበር ገዳዩን በቁጥጥር ሥር ያዋሉት።

ይታከምበት በነበረበት ሆስፒታል ይሠራ የነበረ ግለሰብ ገዳዩ ከአዕምሮ ሕክምና ጣቢያው ሲያመልጥ ለፖሊስ ማሳወቁም ነው የታወቀው።

በዚያው ዓመት መጨረሻ ኬሊ ለወታደራዊው ፍርድ ቤት ሚስቱና ልጁ ላይ የቤት ውስት ጥቃት መፈፀሙን አምኖ ነበር። ከዚያም ለአንድ ዓመት ያህል በአሜሪካ ባሕር ኃይል እስር ቤት ቆይታ አድርጓል።

የአሜሪካ ፌዴራል ምርመራ ቢሮ የገዳዩን ማንነት በደንብ ለማጣራት ስልኩን ለመክፈት እየሞከረ እንደሆነ አስውቋል።

Image copyright Reuters

ገዳዩ ቤተክርስትያኑ ውስጥ ያሉ ሰዎችን በጥይት ከመፍጀቱ አምስት ቀናት ቀደም ብሎ ከልጆቹ ጋር ወደ ቤትክርስትያኒቱ አምርቶ ነበር ሲል ፖሊስ ያክላል።

የዛን ቀን የተነሳው ፎቶ እንደሚያሳየው ገዳዩ ከልጆቹ ጋር እና በጥቃቱ ከሞቱ ሰዎች ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ እንደነበር ነው።

ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ገዳዩ ያለ ርህራሄ ሕፃናትን እንዴት በጥይት ሲገድል እንደነበር ያስታውሳሉ። ከዚያም የተረፉ ሰዎችን እየፈለገ ሲተኩስ ነበርም ብለዋል።

ፖሊስ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያብራራ ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች የራሳቸውን የጦር መሣሪያ አውጥተው ገዳዩን ለመግደል ሲሞክሩ ወደ መኪናው ገብቶ መሄድ ጀመረ።

ሰዎቹ በመኪና እየተከተሉት ሳለ ገዳዩ ከሌላ ተሽከርካሪ ጋር ተጋጭቶ ሕይወቱ ሊያልፍ እንደቻለ አሳውቋል።