ቻይና የገቡት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ጂንፒንግን አድንቀዋል

ቻይና የገቡት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ዢ ጂንፒንግን አድንቀዋል Image copyright AFP/GETTY IMAGES

በእስያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ቻይና ሲገቡ ሞቅ ያለ አቀባበል በቤጂንግ የተደረገላቸው ሲሆን ጂንፒንግ ሰሜን ኮሪያን እየያዘ ያለበት መንገድ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ሆኖም ፕሬዝደንት "ዢ ሰሜን ኮሪያ የኒውክሊዬር መሣሪያዋን ከጥቅም ውጭ እንድታደርግ የበለጠ ጠንክሮ ሊሠራ ይገባል" ሲሉም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

"ቤጂንግ በንግድ ጉዳይ ከአሜሪካ የተሻለች ሆና መገኘቷ ቻይና ተጠያቂ አያደርግም" ሲሉ መናገረቸው ግን ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር።

የሰሜን ኮሪያ ዋነኛ የምጣኔ ሃብት አጋር እንደሆነች በሚነገርላት ቻይና የሚገኙት ትራምፕ ዋነኛ ትኩረታቸውን የኪም ጁንግ ኡን ኒውክሊዬር መሣሪያ ማምከን ላይ አድረገዋል።

ትራምፕና ዢ የ250 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ስምምነት የተፈራረሙ እንደሆነም አሳውቀዋል፤ ነገር ግን ምን ያህሉ አዲስ ምን ያህሉ ደግሞ የቆየ ስምምነት እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።

ከቻይና በፊት በደቡብ ኮሪያ ጉብኝት ያደረጉት ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ ወደ ስምምነት እንድትመጣ ጠይቀው ፒዮንግያንግ አሜሪካንና ሌላውን ዓለም ልትነካ ባትሞክር እንደሚሻላት አስጠንቅቀዋል።

• ዶናልድ ትራምፕ ለሰሜን ኮሪያ፡ "እንዳትሞክሩን"

አልፎም ቻይና ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቋርጥና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ተግባራዊ እንድታደርግም ጠይቀዋል።

Image copyright copyrightREUTERS

ትዊተር የተሰኘው ማሕበራዊ ድር-ገጽ በተከለከለባት ሃገረ ቻይና ከደረሱ በኋላ ትራምፕ ቢያንስ አራት ጊዜ በትዊተር ገፃቸው ላይ ሃሳባቸውን ያሰፈሩ ሲሆን ስለጉዳዩ የተጠየቁት የዋይት ሃውስ ባለሥልጣን "የፈለጉትን ነገር መፃፍ ይችላሉ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ትራምፕ ዕለተ ሐሙስ በቻይና ቤተ-መንግሥት የእራት ግብዣ ካደረጉ በኋላ ወደ ቪየትናም እንደሚሄዱም ይጠበቃል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ