አሽከርካሪ አልባዋ አውቶብስ በመጀመሪያ ቀኗ ግጭት ገጠማት

The Navya Autonom bus

በርከት ያሉ ሰዎችን አሣፍራ በላስ ቬጋስ ከተማ ስትጓዝ የነበረችው አሽከርካሪ አልባዋ አውቶብስ በመጀመሪያ ቀን ሥራዋ ከአንድ ሌላ ተሽከርካሪ ጋር ነው የተጋጨችው።

የተጎዳ ሰው እንደሌለ ያሳወቁት ባለሥልጣናቱ ጥፋቱ በተቃራኒ አቅጣጫ ሲያሽከረክር የነበረ ሹፌር ነው ሲሉ ገልፀዋል።

አሽከርካሪ አልባዋ አውቶብስ በአሜሪካ በሕዝብ መመላለሻ መንገድ ላይ ጥቅም በመስጠት የመጀመሪያዋ መሆን ችላለች።

አውቶብሷ እስከ 15 ሰው ድረስ የማሣፈር አቅም ሲኖራት በሰዓት እሰከ 45 ኪሎ ሜትር መጓዝ ትችላለች።

የላስ ቬጋስ ቃል-አቀባይ ጄስ ራድኬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ገጭቱ ቀላል የሚባል ስለሆነ በቅርብ ቀናት ውስጥ አውቶብሷ ወደ መደበኛ ሥራዋ ትመለሳለች ሲሉ ገልጸዋል።

"አሽከርካሪ አልባዋ አውቶብስ አደጋው ሲያጋጥማት ማድረግ ያለባትን ነው ያደረገችው እሱም መቆም ነው። ነገር ግን የጭነት መኪና አሽከርካሪው ሊያቆም አልቻለም" በማለት ጄስ ገልጸዋል።

አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች ከዚህ በፊትም ግጭት አጋጥሟቸው የሚያውቅ ሲሆን በሁሉም አጋጣሚዎች ስህተቱ የሰው ልጅ ሆኖ ተገኝቷል።

ባለሙዎች እንደሚሉት ከሆነ አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች ሰው ከሚያሽከረክራቸው ተሽከርካሪዎች የበለጠ ደህንነታቸው የተጠበቀ ነው።