የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች ዕጩ፡ ፒየር- ኤመሪክ ኦባመያንግ - ጋቦን እና ቦሪስያ ዶርትሙንድ

ፒየር- ኤመሪክ ኦባመያንግ
አጭር የምስል መግለጫ የቦሪስያ ዶርትሙንዱ ኮከብ 31 ጎሎችን ያስቆጠረው በ32 ጨዋታዎች ነው

ረዥም ዓመት ባስቆጠረው የቡንደስ ሊጋ ታሪክ እ.አ.አ በ20016-17 የውድድር ዓመት ፒየር-ኤመሪክ ኦባመያንግ 31 ጎሎችን አስቆጥሮ ኮከብ ጎል አግቢ በመሆን እስካጠናቀቀበት ዓመት ድረስ አንድም አፍሪካዊ ይህንን ታሪክ አላሳካም።

ጋቦናዊው በዚህ ስኬቱ ጋናዊው ቶኒ ቦሃ በ1990ዎቹ ሁለት ጊዜ ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር በጋራ እኩል ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ የጨረሰበትን ክብር ከማሻሻሉም በላይ በሊጉ ከ30 በላይ ጎሎችን ያስቆጠረ አራተኛው ተጫዋቾች ሆኗል።

በቡንደስ ሊጋው ከአርባ ዓመታት በኋላ ነው አንድ ተጫዋች ከሰላሳ ጎል በላይ ማስቆጠር የቻለው።

በጣም አስገራሚው ነገር ደግሞ የቦሪስያ ዶርትሙንዱ ኮከብ 31 ጎሎችን ያስቆጠረው በ32 ጨዋታዎች መሆኑ ነው። ባለው ፍጥነትና ጎል በማስቆጠር ብቃቱ የሚታወቀው ኦባመያንግ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት በቡንደስሊጋው የዓመቱ ቡድን ውስጥ ተካቷል።

በቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ቤነፊካ ላይ ሃትሪክ (ሶስት ጎሎችን ማስቆጠሩ) መስራቱ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት በጠቅላላው 40 አድርሰውታል።

ቦርሲያ ዶርትሙንድ በጀርመን ካፕ ኢንትራክ ፍራንክፈርትን 2 ለ 1 አሸንፎ ዋንጫ ሲያነሳም አጥቂው አንድ ጎል አስቆጥሯል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
በጀርመን ውጤታማ የሆነው ኦባመያንግ የቢቢሲ ውድድሩን በማሸነፍ የመጀመሪያው ጋቦናዊ ሊሆን ይችላል?

የኦባመያንግ ምርጥ ብቃት በፊፋ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ዕጩ ሆኖ እንዲቀርብ አግዞታል። የ28 ዓመቱ ተጫዋች ከሌላኛው የቢቢሲ የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ዕጩ ሳዲዮ ማኔ ጋር ለባለንዶር ሽልማትም ታጭቷል።

ፋሽን ተከታይ በመሆኑ የሚታወቀው ጋቦናዊው ባለፈው ክረምት ዶርትሙንድን ይለቃል ተብሎ በስፋት ቢጠበቅም እውን ሳይሆን ቀርቷል።

እንደፓሪስ ሴይንት ዠርሜይን እና ማንቸስተር ሲቲ ያሉ ክለቦች ተጫዋቹን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይተው ነበር። እ.አ.አ በ2013 ዶርትሙንድን ከተቀላቀለ ጀምሮ ምርጥ ጎል አስቆጣሪ መሆኑን ያስመሰከረው ኦባመያንግ፤ አያቱ የሚደግፉትን እና በይፋ ምርጫው ያደረገውን ሪያል ማድሪድን የመቀላቀል ህልሙ ግን ሳይሳካ ቀርቷል።

'ኦባ' ባለፈው ዓመት የጀመረውን ጎል የማስቆጠር ብቃት ዘንድሮም እየደገመው ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ስድስት የሊጉ ጨዋታዎች ስምንት ጎሎችን አስቆጥሯል።

በዓለም አቀፍ መድረክ ግን የጋቦኑ አምበል ጥሩ ጊዜን አላሳለፈም። ጋቦን በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ የውድድሩ አዘጋጅ ሆና ከምድብ ድልድሉ ማለፍ ያልቻለች አራተኛዋ ሃገር ሆናለች።

በውድድሩ ላይ ኦባመያንግ በሶስት ጨዋታዎች ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። በጀርመን ውጤታማ መሆኑ ኦባመያንግን የመጀመሪያው ጋቦናዊ የቢቢሲ ሽልማት አሸናፊ ያደርገዋል?

ይህን በመጫን የሚፈልጉትን ተጫዋች መምረጥ ይችላሉ።