የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች ዕጩ፡ ናቢ ኪዬታ - ጊኒ እና ሬድ ቡል ሊፕዚግ

ናቢ ኪዬታ
አጭር የምስል መግለጫ ናቢ ኪዬታ ከራሱ የግብ ክልል እስከተጋጣሚ የግብ ክልል የሚያደርገው አስገራሚ እንቅስቃሴ በተቃራኒ ቡድን ዘንድ እንደ "ሁለት ተጫዋች" ነው አስብሎታል

ናቢ ኪዬታ የአውሮፓውያኑን 2016-17 የውድድር ዓመት በጀርመን ብዙም የማይታወቅ ተጫዋች ሆኖ ቢጀምርም በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ላይ የቡንደስ ሊጋው የዓመቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለመካተት ችሏል። በምርጫው ላይ ከየትኛውም የአማካይ ቦታ ተጫዋች የበለጠ ድምጽ አግኝቷል።

ሬድ ቡል ሊፕዚጎች የ2016-17 አስደናቂ ቡድን ለመሆን ችለዋል። ወደ ቡንደስ ሊጋው ባደጉበት ዓመት ሁለተኛ ሆነው ከመጨረሳቸውም በላይ በሻምፒዮንስ ሊግ የሚያሳትፋቸውን ዕድል አግኝተዋል። በዚህ ውስጥ ደግሞ የጊኒው አማካይ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

ሬድ ቡል ሊፕዚግ ኪዬታን ከኦስትሪያው እህት ቡድኑ ሬድ ቡል ሳልዝበርግ ነው ያስፈረመው። ተጫዋቹ በቡንደስ ሊጋው ተቀይሮ በገባበት የመጀመሪያ ጨዋታ፤ በደቂቃዎች ልዩነት ቦሪሲያ ዶርትሙንድ ላይ የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሮ የራሱንም ሆነ የክለቡን የውድድር ዓመት ምን እንደሚመስል አመላክቷል።

የዓመቱ ምርጥ ጎል ላይ የታጨችውን ጨምሮ በአጠቃላይ ስምንት ጎሎችን አስቆጠሯል። ሰባት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበልም በሊጉ ሶስተኛው ተጫዋች ለመሆን በቅቷል። የ22 ዓመቱ ተጫዋች በመከላከል በኩል ያለው ብቃትም ከፍ ያለ መሆኑን አስመስክሯል።

የኪዬታ ሁለገብ ተጫዋች መሆን ደግሞ ይበልጥ የሚሰብ ነው።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ኪዬታ እንደአርዓያ የሚመለከተው ያያ ቱሬ ያገኘውን የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት ያገኝ ይሆን?

ከራሱ የግብ ክልል እስከተጋጣሚ የግብ ክልል የሚያደርገው አስገራሚ እንቅስቃሴ በተቃራኒ ቡድን ዘንድ እንደ "ሁለት ተጫዋች" ነው አስብሎታል። ፈጣኑን ተጫዋች ማሰለፍ የማይፈልግ አሰልጣኝም የለም።

እንደባለሙያዎች ገለጻ ከሆነ ኪዬታ ካለው ጉልበት በተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ወይም ለጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቶ ለመስጠት የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾችን ለማለፍ የሚያስችለውን ብቃት ተክኗል። ባለፈው ዓመት ኳስ በመግፋት ረገድ ከባየር ሙኒኩ አሪየን ሮበን ጭምር ይበልጥ ነበር።

የሊፕዚግ አሰልጣኝ የሆኑት ራልፍ ሃሰንሃት "በጣም አስፈላጊ" እና ችሎታው ደግሞ በጣም "አስደናቂ" መሆኑን መጥቀሳቸው አስገራሚ አይደለም።

ኮናክሪ የተወለደው ኮከብ ባሳየው ብቃት የተደመሙት ሊቨርፑሎች ለአፍሪካ ተጫዋች ሪከርድ በሆነ 48 ሚሊዮን ፓውንድ በመጪው ክረምት ሊያዘዋውሩት ተስማምተዋል። ሊፕዚጎች ግን እንዳልሸጡትና ዋጋው የውል ማፍረሻው ሂሳብ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኪዬታ በዋነኝነት በክለቡ ውጤታማ ቢሆንም ጊኒ ወደ 2018ቱ የሩሲያ ዓለም ዋንጫ የማለፍ ዕድሏ ጠባብ ነው። አማካዩ ተጫዋች በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ሊቢያ እና ቱኒዝያ ላይ ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

ኪዬታ እንደአርዓያ የሚመለከተው አፍሪካዊ ተጫዋች ያያ ቱሬ ነው። አማካዩ እንደአይቮሪኮስቱ ተጫዋች የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሆኖ ይመረጥ ይሆን?

ይህን በመጫን የሚፈልጉትን ተጫዋች መምረጥ ይችላሉ።