የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች ዕጩ፡ ሞሃመድ ሳላህ - ግብጽ እና ሊቨርፑል

ሞሃመድ ሳላህ
አጭር የምስል መግለጫ ሞሃመድ ሳላህ በተከላካይ መስመሩ ጠንካራነት በሚወደሰው ሊግ 15 ጎሎችን ሲያስቆጥር፤ 11 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ደግሞ አመቻችቶ አቀብሏል

ሞሃመድ ሳላህ ብዙ ጎሎችን ማስቆጠር ቢችልም በግብጽ የሚታወሰው ግን በአንድ ጎሉ ምክንያት ነው። ባለቀ ሰዓት ኮንጎ ላይ አስቆጥሮ ፈርኦኖቹን ከ25 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ እንዲያልፉ ባስቻለበት ጎል።

ግብጽ ሰባት ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን በመሆን ክብረ ወሰን ይዛለች። ሆኖም ከ1990 በኋላ የዓለም ዋንጫ ላይ ተሳትፋ አታውቅም። ጨዋታው 1 ለ 1 ሆኖ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰዓት ሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጭ ትኩረትን የሳበች የፍጹም ቅጣት ምት ግብጽ አግኝታለች።

በተረጋጋ እና በሰከነ መንገድ አስቆጥሮ የ25 ዓመቱ ተጫዋች ቡድኑን ቀዳሚ ለማድረግ ችሏል። በመላው ሃገሪቱ ፈንጠዝያ ከመፈጠሩም በላይ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አል ሲሲ የ80 ሚሊዮን ግብጻዊያንን ተጽዕኖ መቋቋም በመቻሉ አሞካሽተውታል።

ጎሏ የ2017 የፈርኦኖች ንጉስ እንዲሆን አስችሎታል። ያለውን ፍጥነት ተጠቅሞ አንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ለብቻው ሃገሩን የምድቧ የበላይ እንድትሆን በማድረጉ፤ ብሄራዊ ቡድኑ "የሳላህ ግብጽ" እስከመባል ተደርሷል።

ግብጽን ወደ ሩሲያው የዓለም ዋንጫ ካደረሷት ሰባት ጎሎች አምስቱን ያስቆጠረው ሳላህ ነው።

በ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫም አስገራሚ ብቃት አሳይቷል። ግብጽ ካስቆጠረቻቸው አምስት ጎሎች በአራቱ ላይ በመሳተፉ የውድድሩ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለመካተትም ችሏል። ግብጻዊያኑ ለፍጻሜ ደርሰው በካሜሮን ቢሸነፉም ሳላህ በውድድሩ ሁለት ጎሎችን ለማስቆጠር ችሏል።

የግብጻዊው አስደናቂ ብቃት በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። ለሮማ እና ለሊቨርፑልም ጎሎችን አስቆጥሯል።

ባለፈው ሰኔ ሊቨርፑልን ከተቀላቀለ በኋላ አስደናቂ ብቃቱን ቀጥሎ የነሐሴ እና የመስከረም ወር የክለቡ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ለመመረጥም በቅቷል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ሞሃመድ ሳላህ እ.አ.አ ከ2008 በኋላ የቢቢሲን ሽልማት የሚያሸንፍ ግብጻዊ ይሆን?

በክለቡ የመጀመሪያ የፕሪሚር ሊግ ጨዋታ ጎል ከማስቆጠሩም በላይ በአስራ አንድ ጨዋታዎች ሰባት ጎሎችን ከመረብ አሳርፏል። በሻምፒየንስ ሊጉ ደግሞ ያለው ውጤታማነት ከፍተኛ ሲሆን በስድስት ጨዋታዎች አምስት ጎሎችን ለማስቆጠር ችሏል።

እያሳየ ያለው ድንቅ ብቃት ጣሊያን ያደርግ ከነበረው እንቅስቃሴ የቀጠለ ነው። ሮማ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በሊጉ ትልቅ የተባለለትን ውጤት ሲያስመዘግብ የሳላህ ሚና ትልቅ ነበር።

በተከላካይ መስመሩ ጠንካራነት በሚወደሰው ሊግ 15 ጎሎችን ሲያስቆጥር፤ 11 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ደግሞ አመቻችቶ አቀብሏል። በዚህም ከጁቬንቱስ በአራት ነጥብ ዝቅ ብለው ጂያሎሮሲዎቹ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

የቀድሞው የፕሪሚየር ሊጉ ድንቅ ተጫዋች ቲየሪ ሄነሪ "ልዩ" ሲል ያሞካሸው ሳላህ፤ የሃገሩ ልጅ የሆነው መሃመድ አቡትሪካ እ.አ.አ በ2008 የቢቢሲ የዓመቱ የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች ከተባለ በኋላ ሽልማቱን የሚያገኝ የመጀመሪያው ግብጻዊ ይሆን?

ይህን በመጫን ሚፈልጉትን ተጫዋች መምረጥ ይችላሉ።