ኦባማ ፍርድ ቤት ሊያገለግሉ ቢመጡም አገልግሎትዎ አያስፈልግም በሚል ተሰናበቱ

ኦባማ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ቺካጎ በሚገኘው ፍርድ ቤት እንደ ጁሪ (በአሜሪካ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ፍርድ የሚቀመጡ ሰዎች) ሆነው ቢቀርቡም ዳኛው ለማገልገል ጥያቄ ሳይቀርብልዎት ነው የመጡት በሚል አሰናብተዋቸዋል።

የሳቸውንም መምጣት ተከትሎ ብዙዎች ዳሊ ሴንተር በሚባለው የማዘጋጃ ህንፃ ላይ 44ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለማየት በጉጉት ተሰብስበው እየጠበቁት ነበር።

ሳይመደቡም ፍርድ ቤት በጁሪነት መሄድ የተለመደ ቢሆንም ፤ ለኦባማ መሰናበታቸው ኦፊሴያላዊ ምክንያት አልተሰጠም።

ኦባማ ሮብ ጥዋት ፍርድ ቤት የደረሱ ሲሆን ወደ ግማሽ ቀንም ላይ ተመልሰዋል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት የህግ ፕሮፌሰር የነበሩ ሲሆን ቺካጎ ውስጥም መኖሪያ ቤት አላቸው።

በጁሪም ውስጥ ለማገልገል ከሀገሪቷ 17 ዶላርም ወይም 430 ብር ይከፈላል።

ኦባማ ከቤታቸው ኬንውድ አካባቢ ወጥተው በመኪናቸው ሲሄዱ የተለያዩ ሚዲያዎች በሄሊኮፕተሮች እያንዣበቡ እየቀረፁዋቸው ነበር።

ያለ ከረባት ጃኬት ለብሰው የተገኙት ኦባማ 17ኛ ፎቅ ላይ ተገኝተው ከሌሎች የፍርድ ቤቱ ሰራተኞች ፣ ጋዜጠኞች ጋር ተገናኝተዋል።

በፍርድ ቤቱ ለረዥም ጊዜ ያልቆዩ ሲሆን፤ዳኛውም በዘፈቀደ ኦባማን መርጠው አገልግሎታቸው እንደማያስፈልግ ነግረው አሰናብተዋቸዋል።

ከመሄዳቸውም በፊት ኦባማ ጁሪውን ሊያገለግሉ ለመጡት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።

አንዳንዶች የኦባማን መፅሀፍ በቦታው ይዘው በመምጣት እንዲፈርሙላቸው የጠየቁ ሲሆን ፤የፍርድ ቤቱን ሰራተኞች ጨምሮ ሌሎችም አብረዋቸው ፎቶ ተነስተዋል።

ለጁሪነት የመጣች አንደኛዋ ደስታዋን መቆጣጠር አቅቷት የነበረ ሲሆን፤ ለአካባቢው ጋዜጣም የፕሬዚዳንቱን እጅ በጨበጠችበት ወቅት "እንደ ቅቤ እንደቀለጠች" ተናግራለች።

የኦባማ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ካቲ ሂል እንደተናገሩት "የቀድሞው ፕሬዚዳንት በሀገሪቷ ዲሞክራሲ ውስጥ ከስልጣን በላይ ቀዳሚው ነገር ዜጋ መሆንን አሳይተዋል። በጁሪ ውስጥ ማገልገልን ደግሞ ዋናው የዜግነት ግዴታ ነው" በማለት ተናግረዋል።

በመጀመሪያ አመታት የፕሬዚዳንትነታቸው ወቅት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠይቀው የነበረ ሲሆን ከፍርድቤቱም ቀጠሯቸውን ማስተላለፍ እንዲችሉ ፈቃድ አግኝተው ነበር።

እንደ ምክንያትነትም ያቀረቡትም በኢራቅ ከምትገኘው የኩርዲስታን ግዛት ፕሬዚዳንት ቀጠሮ ስለነበራቸው ነው።

ከሁለት ዓመታት በፊት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ጁሪ እንዲያገለግሉ በዳላስ ቴክሳስ ተጠርተው የነበረ ሲሆን ፤ከሌሎች ጁሪ ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር ፎቶ ተነስተው በማጋራታቸው ተሰናብተዋል።

ከአራት አመታትም በፊት በኒው ዮርክ የተደራጁ ቡድኖች የተኩስ ልውውጥን አስመልክቶ በነበረ ክስ ላይ በጁሪነት ሊያገለግሉ የመጡት ቢል ክሊንተንም ተሰናብተው ነበር።