“በቀናት ውስጥ ወደ ሊባኖስ እመለሳለሁ” - ሳይድ ሃሪሪ

Lebanese watch an interview with Saad Hariri at a coffee shop in Beirut Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የጠቅላይ ሚንስትሩ ስራ መልቀቅ በሊባኖስና በአካባቢው ሃገራት መደናገጥን ፈጥሯል

የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚንስትር ሳይድ ሃሪሪ "በቀናት ውስጥ" ወደ ሃገራቸው በመመለስ በይፋ መልቀቂያቸውን እንደሚያስገቡ አስታወቁ።

ባለፈው ሳምንት ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ካስታወቁ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሪያድ ለፊውቸር ቲቪ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የካቢኔ ባልደረባቸው በቁጥጥር ስር ውለው ነው ሲሉ የሰጡትን አስተያየት ሃሪሪ ውድቅ አድርገውታል።

በኢራን የሚታገዘው የሂዝቦላህ እንቅስቃሴ በራሳቸውና በቤተሰባቸው ደህንነት ላይ ስጋት በማሳደሩ ለመልቀቅ መወሰናቸውን ተናግረዋል።

ሌሎች ሃገራት ሊባኖስን ማዕከል በማድረግ ተዘዋዋሪ ጦርነት ውስጥ እንዳይገቡ አሜሪካና እንግሊዝ አስጠንቅቀዋል።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የጠቅላይ ሚንስትሩ ምስሎች በቤሩት ተሰቅለዋል። ይሄኛው "ሁላችንም ሳይድ ነን" ይላል

የሱኒ መሪ የሆኑትና በንግድ ስራ የሚተዳደሩት ሃሪሪ እ.አ.አ ህዳር 2016 ነበር ለሊባኖስ መንግስት ዕጩ ሆነው የቀረቡት።

"ስራዬን ለቅቄያለሁ። በቅርቡ ወደ ሊባኖስ በማቅናት ህገ-መንግስቱ ባስቀመጠው መሠረት ስራዬን እለቃለሁ" ብለዋል በሰጡት ቃለመጠይቅ።

"መልቀቄ ለሊባኖስ የማንቂያ ደወል ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ኢራንና የሺአ ፓርቲው ሂዝቦላህ በጋራ በመሆን ሊባኖስን በመቆጣጠር አካባቢውን ወደ አለመረጋጋት ሊከቱት ነው ሲሉ ባለፈው ሳምንት ከሪያድ ተናግረው ነበር።

"እንደ ፓርቲ ከሂዝቦላህ ጋር ችግር የለብኝም። ችግር ያለብኝ ሂዝቦላህ ሃገር ሲያፈራርስ ነው" ሲሉ በቴሌቭዥን ባደረጉት ቃለመጠይቅ ተናግረዋል።

ከአካባቢያዊ ግጭት ነጻ መሆን የሚለውን የሊባኖስ ፖሊሲ ሂዝቦላህ ካከበረ የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን ሊቀለብሱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ሳዑዲ አረቢያ ሃሪሪን በቁጥጥር ስር አውላቸዋለች በሚል ኢራን እና ሂዝቦላህ ይከሳሉ።

ሃሪሪ ግን በሃገሪቱ በነጻነት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተናግረዋል። "እዚህ ነጻ ነኝ። ነገ መጓዝ ከፈለኩኝ እችላለሁ" ብለዋል።

የሃሪሪ አባት የነበሩት የሊባኖስ የቀድሞው መሪ ራፊቅ ሃሪሪ እ.አ.አ በ2005 መኪና ላይ በተጠመደ ቦንብ ህይወታቸው አልፏል።

እንደ ሃሪሪ ገለጻ ከሆነ የአካባቢው ዋና ችግር "ኢራን በአረብ ሃገራት ጣልቃ መግባቷ ነው።"

"ሊባኖስ ከአረብ ሃገራት ጋር በሚኖራት ፍጥጫ ሃላፊነት መውሰድ አልፈልግም" ሲሉ ሃሪሪ ሰሞኑን ከየመን ወደ ሪያድ የተወነጨፈውን ሚሳኤል ጠቅሰው አስታውቀዋል።

ሳዑዲ መራሹ ጥምር ጦር ከሪያዱ ጥቃት ጀርባ ኢራንና የሊባኖሱ ሂዝቦላ ከሁቲ አማጺያን ጋር ተባብረዋል በሚል ይከሳል።

"ካለምንም መዘግየት" ሃሪሪ ወደ ሊባኖስ እንደሚመለሱ ያላቸውን ተስፋ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቦሪስ ዮንሰን ገልጸዋል።

የሊባኖስ ሉዓላዊነት ሊከበር ይገባል ያሉት ዮንሰን "ሃገሪቱ ለተዘዋዋሪ ጦርነት መጠቀሚያ መሆን የለባትም" ሲሉ ተናግረዋል።