የዛፍ ልጥ እንዴት የወረቀት ገንዘብን ፈጠረ?

Marco Polo Image copyright Getty Images

ከ750 ዓመታት በፊት የቬኑሱ ነጋዴ ማርኮ ፖሎ በቻይና ያደረገውን ጉዞ የሚተርክ አስገራሚ መጽሃፍ ጽፎ ነበር ።

''የዓለም ትንግርቶች'' በተሰኘው በዚህ መጽሃፍ ማርኮ ታዝቤያለሁ ያላቸውን አስገራሚ የውጭ ሃገር ልምዶችን አካፍሎበታል።

ነገር ግን ከሁሉም የተለየበትን አንድ ክስተት አስተውሎ ነበር።

ማርኮ የዘመናዊውን ኢኮኖሚ መሰረት የለወጠውን የወረቀት ገንዘብ ፈጠራ እማኝ ለመሆን ከታደሉ የመጀመሪያዎቹ አውሮፓውያን አንዱ ሆነ።

በእርግጥ ዋናው ማርኮን የሳበው ወረቀቱ አልነበረም ምክንያቱም ዘመናዊው ገንዘብ በተለምዶ የወረቀት ይባል እንጂ የሚሰራው ከጥጥ፣ ከፋይበርና ከፕላስቲክ ነው።

የያኔው የቻይና ገንዘብ ግን ከዛፍ ግንድ በተሰራ ዝርግ ልጥ ላይ ቀይ ማህተም አርፎበት በዚያን ጊዜ በነበረው ንጉስ ኩብላይ ካን ማረጋገጫ ካገኘ በኋላ ጥቅም ላይ የሚውል ነበር።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ኩብላይ ካን ማረጋገጫ ያረፈበት የዛፍ ልጥ ገንዝብ ሆኖ እንደሚያገለግል አወጁ

የማርኮ ፖሎ መጽሃፍ አንዱ ምዕራፍ "ታላቁ ካን የዛፍ ግንድን በመጠቀም ከወረቀት መሰል ነገር የገንዘብ ዝውውርን በመላ ሃገሪቱ እንዴት ይፈጽሙ ነበር?'' የሚል ርዕስ ነበረው።

ይህ ገንዘብ ከምንም ቢሰራ ዋጋው የሚወደደው በተሰራበት እቃ ውድነት ምክንያት አይደለም።

ይልቅስ ዋጋው የሚወሰነው የመንግሥት ባለስልጣናት በወሰኑለት ልክ ነው።

ምጡቁ ስርዓት

የወረቀት ገንዘብ አንዳንድ ጊዜ "የፊያት" ገንዘብ ይባላል። በላቲን ፊያት ማለት "ይደረግ" እንደማለት ነው።

ታላቁ ካንም ህጋዊ ማህተም ያለበት የዛፍ ልጥ ገንዘብ ሆኖ እንደሚያገለገል ይፋ አደረጉ። እናም ገንዘብ ይደረግ ተባለ።

የዚህ ስርዓት ፈጠራ ማርኮ ፖሎን አስደምሞት ነበር። በወቅቱ የወረቀት ገንዘብ የሚሰራጨው ራሱ ልክ ወርቅና ብር እንደሆነ ተደርጎ ነበር።

በእርግጥ ማርኮ ፖሎ ስለዚህ ገንዘብ ሲሰማ ጉዳዩ አዲስ ነገር አልነበረም። ይህ የገንዘብ ዓይነት ከ300 ዓመታት በፊት ነበር በቻይና ሲቹዋን የተዋወቀው።

ከሌሎች ሀገራት አንዳንዴም ካልተረረጋጉት ጋር የምትዋሰነው ሲችዋን ፈር ቀዳጅ ግዛት ነበረች።

የቻይና ገዢዎች እንደብርና ወርቅ ያሉ ውድ ንብረቶች ወደ ውጭ ሀገራት ሰርገው እንዲገቡ ስላልፈለጉ ያልተለመደ ህግ አወጡ።

ሲችዋን ከብረት በተሰሩ ሳንቲሞች እንድትገበያይ ወሰኑ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በቻይና ሶንግ ስርወ መንግስት(960-1279) ያገለግሉ የነበሩት ሳንቲሞች በ2005 ተገኝተዋል

ብረት በእርግጥ ለአሰራር ብዙም ክፉ የሚባል አልነበረም።

አንድ መዳፍ ለሚሞላ 50ግራም የብር ሳንቲም አቻ ግብይት የራስዎን ክብደት ያክል የሚመዝን የብረት ሳንቲሞች ለሆኑ ይችላሉ።

እንደ ጨው ያሉ ቀለል ያሉ ምርቶች እንኳን ዋጋቸው በብረቱ ክብደት ልክ ይወሰናል።

እናም ሸቀጦችን ለመግዛት በቦርሳዎ ገንዘብ ይዘው ሄደው ገብይተው ሲመለሱ የሚሸከሟቸው የብረት ሳንቲሞች ከገዟቸው ሸቀጦች የበለጠ ክብደት ይኖራቸዋል።

የሲቹዋን ነጋዴዎችም ይኸው ችግር ገጥሟቸው ነበር።

እናም የወርቅና የብር ሳንቲሞችን መጠቀም ሕገወጥ ስለነበረ፣ የብረት ሳንቲሞች ደግሞ ለአያያዝ ስለማይመቹ አማራጭ መንገዶችን ፍለጋ መማተር ጀመሩ።

ይህ አማራጭ 'ጂያኦዚ' ወይም ' የክፍያ ልውውጥ' የሚል ስያሜ ነበረው።

ከፍተኛ ክብደት ያላቸውን የብረት ሳንቲሞች ከመሸከም ይልቅ ነጋዴዎች ክፍያቸውን ሌላ ጊዜ ሲመቻቸው እንደሚከፍሉ ቃል ይገባሉ።

ይህ በቂና ቀላል ሃሳብ ነበር። ነገር ግን ከዚሁ ጋር አንድ የኦኮኖሚ አስማት ተፈጠረ። በነዚህ 'ጂያኦዚ'ዎች የነጻ ግብይት ተጀመረ።

ለምሳሌ አንድ ሰው ለሌላኛው እቃ አቅርቦ ለክፍያው ጆያኦዚ ተቀብሎ ራሱ ለመሸመት ቢወጣ ክፍያውን በብረት ሳንቲሞች ከመፈጸም ይልቅ ከሌላኛው ሰው የተቀበለውን '' ጂያኦዚ'' ለሌላኛው ሻጭ በማስተላለፍ ይፈጽማል ማለት ነው።

የወረቀት ገንዘብ ውልደት

ይህ ከሰው ሰው መተላለፍ የሚችል የክፍያ ቃልኪዳን ሂደት ኋላ ቀር ቢሆንም የቀድሞ መገበያያ ገንዘብ ነበር።

በተለይም ደግሞ በ'ጂያኦዚ' እቃ ለሸመተው የመጀመሪያው ሰው በጣም ጥሩ ዜና ነው።

ምክንያቱም ሰዎች የእርሱን ጂያኦዚ ለሚሸምቱት እቃ መክፈያነነት እስከተጠቀሙበት ድረስ እርሱ የብረት ሳንቲም መጠቀም አያስፈልገውም።

የእርሱ ጂያኦዚ ከሰው ሰው መተላለፉ እስካልተቋረጠ ድረስ ወለድ የማይታሰብበት ብድር እንደወሰደ ሰው ይቆጠራል።

ምናልባትም መቼም ቢሆን እንዲከፍል ላይጠየቅ ይችላል።

Image copyright British Library Board Or.12380/2286/22
አጭር የምስል መግለጫ በአውሮፓውያኑ 1260ዎቹ መጀመሪያ የታተመ የባንክ ኖት

እናም የቻይና ባለስልጣናት ይህ ሂደት ግለሰቦችን እንጂ እነርሱን ተጠቃሚ እንደማያደርግ በመረዳታቸው የጂያኦዚን ስርጭት መቆጣጠር ጀመሩ።

እንዲያውም ጂያኦዚን በመከልከል ሁሉንም ንግዶች በእነርሱ ቁጥጥር ስር አደረጉ።

ዘመናዊ እድገት

ጂያኦዚ በአከባቢያዊና በዓለማቀፍ ደረጃ የሚተገበር ትልቅ መገበያያ ነበር።

ከብረት ሳንቲሞች በተቃራኒ ለአያያዝ ምቹ ስለሆኑ ለጨረታ ክፍያዎችም ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር።

መጀመሪያ በመንግሥት የተረጋገጡ ጂያኦዚዎች ሳንቲምን ተክተው ለግብይት እንዲውሉ ተፈቅዶ ነበር፤ ልክ የግል ጂያኦዚዎች ያገለግሉ እንደነበረው ማለት ነው።

ወረቀቶቹ ትክክለኛው ዋጋ ስለሰፈረባቸው እንደ ተምሳሌቶች ይቆጠሩ ነበር።

ሆኖም መንግስት ብዙም ሳይቆይ መሰረታዊ ሃሳቡን በማቆየት ነገር ግን ጂያኦዚን እንደገንዘብ መጠቀምን በመተው ወደ ፊያት ስርዓት ለወጠው።

በዚህ ስርዓት አሮጌ ጂያኦዚን ያላቸው ወደመንግሥት ግምጃ ቤት በማምጣት ወደአዲስና ጠንካራ ጂያኦዚ ይቀይሩበታል።

ይህ ደግሞ በጣም ዘመናዊ እድገት ነበር።

አሁን የምንጠቀምባቸው የወረቀት ገንዘቦች በማዕከላዊ ባንኮች የተፈጠሩበት ሃሳብ መነሻም ይህ አሮጌ ገንዘብን በአዲስ ለመቀየር የገቡት ቃል ነው።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በ1699 የእንግሊዝ ባንክ ማረጋገጫ ያረፈበት የባንክ ኖት

ገደብ ያጣ ፍላጎት

ፊያት ገንዘብ ለመንግሥታት ፈተናም አስከትሎ ነበር። የሚከፍለው ክፍያ ሲኖረው ማድረግ የሚጠቀምበት ተጨማሪ ገንዘብ ማተም ብቻ ነበር ።

ነገር ግን ይህ ገደብ ያልነበረው ፍላጎት የኋላ ኋላ ለመቋቋም በሚቸግር መልኩ እያደገ መጣ።

ሆኖም ተመሳሳይ መጠን ላላቸው ሸቀጦችና አገልግሎቶች ተጨማሪ ገንዘብ እየቀረበ ሲመጣ ዋጋውም መጨመር ጀመረ።

የሶንግ ስርወ መንግስት ለብዙ ጂያኦዚዎች ማረጋጋጫ ሰጥቶ ስለነበር የማጭበርበሪያ መንገዶችም ተፈጠሩ።

እናም በ11ኛው ክፍለ ዘመን ጂያኦዚ በተፈጠረ በጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ የመግዛት አቅሙ እየተዳከመና ከቀድሞ ዋጋው 10 በመቶው ብቻ የሚሸመትበት ሆነ።

ሌሎች ሀገራትም ከዚህ ለባሰ ችግር ተጋለጡ።.

ዌይማር ጀርመንና ዚምባብዌ በርካታ ቁጥር ያለውን ገንዘብ በማተማቸው ዋጋቸው አሽቆልቁሎ ኢኮኖሚያቸው ለፈራረሱት ምሳሌዎች ናቸው ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ዚምባቡዌ ከፍተኛ የዋጋ ግሸበትን አስተናግዳለች

ሃንጋሪ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1946 የዓለምን ሪከርድ የሰበረ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን አስተናገደች።

በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎችም የነገሮች ዋጋ በእጅጉ ማሻቀብ ጀመረ።

በቡዳፔስት በሚገኝ ሻይ ቤት ገብተው ቡና ሲጠጡ ክፍያውን መጀመሪያ ካልከፈሉ ጠጥተው እስኪጨርሱ እንኳን ዋጋው ሊጨምር ይችላል።

የወርቅ ግብይት

ይህ ብዙም ያልተለመደ ግን በጣም አስጨናቂ የነበረው ሁኔታ የኢኮኖሚ አድገት አቀንቃኞችን ፊያት ገንዘብ የተረጋጋ ኢኮኖሚን ሊፈጥር እንደማይችል አሳመናቸው።

የወረቀት ገንዘብ ሁልጊዜም በአነስተኛ የከበረ ማዕድን መቀየር የሚቻልበት የወርቅ ግብይት ተመልሶ እንዲተገበርም ፍላጎት አሳዩ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ወርቅ ለብዙ ሺዎች ዓመታት በመገበያያነት ሲያገለግል ቆይቷል

ሆኖም ዋነኞቹ የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች የገንዘብ አቅርቦትን ከወርቅ ጋር ማስተሳሰር ጥሩ ሃሳብ እንዳልሆነ ይሞግታሉ።

ሁልጊዜም የማዕከላዊ ባንክ ባለሞያዎች ተገቢውን ገንዘብ ብቻ ያትማሉ ብሎ መተማመን ባይቻልም ማዕድን አውጪዎች የሚያሰፈልገውን ወርቅ ቆፍረው ያወጣሉ ብሎ ከመጠበቅ የተሻለ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በአውሮፓውያኑ 2007 ከተሰከተው የገንዘብ ቀውስ በኋላ የአሜሪካ የፌደራል መጠባበቂያ ክምችት በትሪሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ግሽበትን ሳይፈጥሩ ወደ ኢኮኖሚው ማስገባት ችሏል።

እነዚህ ዶላሮች በዓለማቀፉ የባንክ ስርዓት አማካኝነት ከኮምፒተሮች ጥቂት የመተየቢያ ቁልፎችን በመጫን ብቻ የተፈጠሩ ናቸው።

እናም በአርቆ አሳቢው ማርክ ፖሎ አገላለጽ '' ታላላቆቹ ማዕከላዊ ባንኮች የኮምፒተር አሃዞችን በመጠቀም እንደወረቀት ያለ ነገር እየፈጠሩ በገንዘብነት ያስተላልፉታል''

ቴክኖሎጂ ይቀየራል፤ ገንዘብ የሚተላለፍበት ሂደት ግን ሁሌም እያስደነቀን ይቀጥላል።