ሐረርና ጀጎልን በምስል

የጀጎሏ ሐረር በአነስተኛ የመሬት ስፋት በርካታ ጎብኚዎችን ከሚያስተናግዱ ጥቂት የዓለማችን ከተሞች አንዷ ናት፤ ከ1000 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የከተማዋ ታሪክ ቅርሶቿም እንዲበዙ እድል ፈጥሮላታል። የጀጎል ግንብና አምስቱ በሮች፣ የወርቅ ሳንቲሞች፣ ረጅም እድሜን ያስቆጠሩ መስጊዶች ፣ የስነ-ሕንፃ፣ የታሪክን አሻራ የሚያንፀባርቁ የቤት ውስጥ ዕቃዎች ቱሪስትን ከሚስቡት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።

Image copyright Empics

በፈረንሳዊው ጸሃፊ አርተር ራምቦ የተሰየመው ሙዚየም አንዱ ነው። በሙዚየሙ ከረጅም ዓመታት በፊት የተነሱ የሐረር ከተማ ፎቶዎችና በከተማዋ ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን ያካተቱ ክፍሎች ኣሉበት። አርተር ራምቦ 1880 ወደሃረር ከተማ በመሄድ በ11 ዓመት ቆይታው ለ120 ዓመታት መቆየት የቻሉ ፎቶዎችን አንስቷል። የዚህ ሙዚየም ግንባታ ጂዋጅ በሚባል ህንዳዊ እንደታነጸ መረጃዎች ያመለክታሉ።

አፍላላ ዉፋ ከሸክላ የሚሰሩ የባህላዊ እቃዎች ሲሆኑ በቁጥርም አራት ናቸው፤ በሐረሪ ብሄረሰብ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በቅደም ተከተል ይቀመጣሉ። እያንዳንዳቸውም የየራሳቸው አገልግሎት አላቸው። የመጀመሪያው የእናት ባንክ ሲሰኝ ባል ለቤት ወጪ የሚሆነውን ገንዘብ የሚያስቀምጥበት ፤ሁለተኛው ባህላዊ መድኃኒቶችን ማስቀመጫ፤ ሶስተኛው የመድኃኒቶችና የእህል ዘሮች ይቀመጥበታል። አራተኛው ደግሞ የግብርና የተለያዩ ክፍያዎች ደረሰኞችን የሚይዝ ነው።

ቆሪ ሃዳ- በሠርግ ወቅት እናት የምትድራት ልጇን ወደ አማቶቿ ቤት ሂዳ በመልሱ እስክትመጣ ድረስ የሚጠቅሟትን ዝሁቅ፣ አቅሌል፣ መቅሊ እና ሌሎች ምግቦችን ስንቅ የምትቋጥርበት ነው። እስከ 25 ኪሎግራም የሚመዝን ምግብ የመያዝ አቅም ሲኖረው፤ እነዚህንም የባህል ምግቦች ይዘው የሚሄዱት ሰዎች የሐረርን ባህል በደንብ የሚያወቁ ሰዎች መሆን አለባቸው።ይህ ከዋንዛና ከሌሎች የዛፍ አይነቶች የሚሰራው ቆሪ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ወደልጅቱ ቤተሰቦች የተለያዩ ስጦታዎች ተደርገውበት ይመለሳል።

በሐረሪ ባህል ቤቶች ውስጥ የመደብ መቀመጫ ትልቅ ቦታ አለው። በአንድ ቤት ውስጥ አምስት መደቦች የሚሰሩ ሲሆን ሰዎች በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ የሚያመለክቱ ናቸው። እውቀት፣ ጾታና እድሜን መሰረት ያደርጋሉ። ከፍተኛ የኃይማኖት እውቀት ያላቸው ምሁራን ከፍ ያለው መደብ ላይ ሲቀመጡ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችም በሚዘጋጅላቸው መደብ ላይ ይቀመጣሉ። አምስቱ መደቦች ስያሜያቸው በሃደሬ ቋንቋ ''አሚር ነደብ'' ''ግድር ነደብ'' ''ጥት ነደብ'' ''ጉት ነደብ'' እና ''ገብትሄር ነደብ'' ይባላሉ።

እንዳሁኑ ጫማ በዘመናዊ መልኩ መሰራት ከመጀመሩ በፊት የሐረሪ ህዝብ ከእንጨትና ከቆዳ የሚሰሩ ጫማዎችን ይጫማ ነበር። ከእንጨት የሚሰራው ጫማ ቤት ውስጥ ለመንቀሳቀስ የሚያገለግል ሲሆን ከቆዳ የሚሰራው ደግሞ ለረጅም ጉዞ ያገለግላል።

የጀጎል ግንብ በ1551/52 በንጉስ/አሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ እንደተገነባ የታሪክ መዛግብት ያመላክታሉ። ይህ ግንብ ከምድር 4 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን ወርዱ ደግሞ ከ50-75 ሴንቲሜትር ይሰፋል። ግንቡ አምስት በሮች ያሉት ሲሆን ውሃ ያለበትን አቅጣጫም ለማመልከት የተሰሩ ናቸው።

ከአምስቱ በሮች እንዱ ከረ ፈልአና ሲሆን ስያሜውን ያገኘው በዚህ ስም ወደምትጠራ መንደር ስለሚወስድ ነው ይባላል። ሐረሪዎች ደግሞ ይህንኑ በር ከረ አሱሚ ብለው ይጠሩታል፤አሱሚ በሃደሪኛ በርበሬ ማለት ሲሆን ፊት ለፊት ከሚገኘው ቀይ ቀለም ያለው ወንዝ የተወሰደ ነው ይላሉ።