የሮሂንጃ ጉዳይ፡ የምያንማር ጦር ከደሙ ነፃ ነኝ እያለ ነው

Hundreds of thousands of Rohingya people are now living in refugee camps like this one in Bangladesh Image copyright DIBYANGSHU SARKAR

የምያንማር ጦር የውስጥ ምርመራዬ ውጤት ነው ያለውን ሪፖርት ይፋ ባደረገበት መግለጫ በሮሂንጃ ሙስሊሞች ግድያ ውስጥ እጄ የለም ሲል አስታውቋል።

የምያንማር ጦር የማንኛውንም የሰላማዊ ሮሂንጃ ሙስሊም ቤት አላቃጠለም፤ የሰው ሕይወትም አላጠፋም ሲል መግለጫው ያትታል ።

ጦሩ ያወጣው መግለጫ የቢቢሲ ጋዜጠኛና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካረጋገጡት ጋር እጅግ የሚጋጭ ሆኖ ተገኝቷል። የተባበሩት መንግሥታት ሁኔታውን "የዘር ጭፍጨፋ" ሲል መወንጀሉ የሚታወስ ነው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለምአቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅት "ሪፖርቱ ተለውሶ የወጣ ሃሰት" ሲል ይወቅሳል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወደቦታው ገብቶ ሁኔታው እንዲያጣራም ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል ።

መገናኛ ብዙሃን ወደ ቦታው እንዳይገቡ በጥብቅ በተከለከለበት ሁኔታ ወደ ቦታው መግባት የቻለው የደቡብ ምስራቅ ቢቢሲ ዘጋቢ ጆናታን ሄድ የቡድሂስት እምነት ተከታዮች በምያንማር ጦር ታግዘው የሮሂንጃ ሙስሊሞችን ቤት ሲያቃጥሉ መመልከቱን ዘግቧል።

ከነሐሴ ጀምሮ በተፈጠረው ግጭት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ምያንማርን ጥለው መሰደዳቸው ተዘግቧል።

ወደ ባንግላዴሽ መግባት ከቻሉት መካከል በጥይት የተመቱ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ሁሄታውን ሲያስረዱ የምያንማር ጦርና የቡድሂስት እምነት ተከታዮች ሰላማዊ ሮሂንጃዎችን ሲገድሉና መኖሪያቸውን ሲያቃጥሉ ነበር።

ጦሩ በፌስቡክ ገፁ ባሰፈረው መግለጫ ግጭቱ በተከሰተበት የሚኖሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ቃል መቀበሉንና ነዋሪዎቹም ጦሩ ምንም ዓይነት ወንጀል አለመፈፀሙን ማረጋገጣቸውን አትቷል።

"የምያንማር ጦር ሰላማዊ ሰው አልተገደለም፤ ፆታዊ ጥቃት አልተፈፀመም፤ እሥራትም ሆነ ድብደባ አልተፈፀመም፤ ስርቆትም አልተካሄደም፤ መስጊዶችንም ሆነ ቤቶችን አላቃጠለም እንዲሁም ማንንም አላፈናቀለም" በማለት ሪፖርቱ ያትታል።

ለተቃጠሉ ቤቶችና ለተሰደዱ ሰዎች ተጠያቂው 'ቤንጋሊ' እየተባለ የሚጠራው የሮሂንጃ አሸባሪ ቡድን ነው ሲልም ይኮንናል።

Image copyright AFP/ GETTY IMAGES

ታማኝነት የጎደለው ሪፖርት

የቢቢሲው ዘጋቢ ጆናታን ሄድ የምርመራ ውጤቱ ትክክለኛውን እና ታማኝ የሆነውን ሪፖርት ለማግኘት ጊዜ የሚወስድ ነው ሲል ሁኔታውን ከታች እንዳለው ይተነትናል።

በአስገራሚ ሁኔታ ጦሩ ከእያንዳንዱ ውንጀላ ራሱን ማግለሉ ሪፖርቱን ኢ-ተአማኒ ያደርገዋል። አልፎም ምርመራውን ያካሄደው ራሱ ተወቃሹ የምያንማር ጦር መሆኑ ለኢ-ተአማኒነቱ ሌላ መሠረት ነው።

ከየትየለሌ የሮሂንጃ ሙስሊሞች የሚሰማው ተቃራኒ መሆኑና ወደ ባንግላዴሽ ከሚገቡት መካከል በመቶ የሚቆጠሩ በጥይት የቆሰሉ መሆናቸው የሪፖርቱን ተአማኒነት ዝቅ የሚያደርግ ሌላ መለኪያ ነው።

ጦሩ ከባድ መሣሪያ መጠቀሙን ቢክድም የምያንማር መንግሥት ባዘጋጀው ጉዞ ላይ ተሳፍሬ ወደ ግጭቱ ወደተከሰተበት ረካይን ግዛት በተጓዝኩበት ወቅት የከባድ መሣሪያ ድምፅ ሰምቼ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የተለያዩ የመብት ተሟጋች ቡድኖች መኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ባንግላዴሽ የገቡ የሮሂንጃ ሙስሊሞችን ቃል ተቀብለው ያወጧቸው ዘገባዎችም የምያንማር ጦር ጥቃት እንደፈፀመ እንጂ ከደሙ ነፃ እንደሆነ የሚያሳዩ አይደሉም ሲል ዘጋቢው ትንታኔውን ይደመድማል ።

በቀጣይ. . .

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ቃል-አቀባይ እንደሚናገሩት "የምያንማር ጦር ተጠያቂነትን እንደማያስረግጥ በጣም ግልፅ ነው።"

"አሁን ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጣልቃ ገብቶ ይህንን ግፍ ማስቆምና ጥቃት አድራሾችንም ለፍርድ ማቅረብ አለበት" ሲሉ ቃል-አቀባዩ ያሰምራሉ ።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሬክስ ታይለርሰን ሮብ ዕለት ምያንማርን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።

ተያያዥ ርዕሶች