ከስደት ወደ ባለሃብትነት-የኢትዮጵያዊው የስደት ኑሮ በአውስትራሊያ

Obbo Daawiti konkoolaataa ittiin abaaboo bakka qonnaatii dedeebisan waliin Image copyright AP

አቶ ዳዊት ኢተፋ ይባላሉ። በስዕል ተሰጥኦ ያላቸውና በኢትዮጵያ በነበሩበት ጊዜ በተለያዩ ክፍለሃገራት በመዘዋወር ሲሰሩ የቆዩ ናቸው። አቶ ዳዊት የሚያከብሯት ጥበብ ከሚወዷት ሃገራቸው እንዲወጡም ምክንያት ሆነች። እንዴት? ይኸው የአቶ ዳዊት አስደናቂ የሕይወት ጉዞ ከራሳቸው አንደበት።

ከሀገሬ የወጣሁት እ.አ.አ በ1980 ነው። እዚህ ውሳኔ ላይ እንድደርስ ያደረጉኝ የተለያዩ ምክንያቶች ነበሩኝ።

አንደኛ በኢሉባቡር ክፍለሃገር 'እንባ' የተሰኘ ስዕል ሰራሁና ባሮ በሚባል ሆቴል ውስጥ ሰቀልኩት። ''የሆቴሉ ባለቤት በጣም ሲረዱኝ የነበሩና የተከበሩ በመሆናቸው የእርሳቸውንም ፈቃድ እንኳን ሳልጠይቅ እንደስጦታ አድርጌ ነበር የሰቀልኩት።

ከዚያም መንግሥትን የሚያሳፍርና የሚያዋርድ የፖለቲካ ሥራ ነው ተባልኩና በአካባቢው ባለስልጣናት ፊት ቀረብኩኝ። በእስር ቤት ውስጥ ለ1 ወር ስቃይና መከራ ካደረሱብኝ በኋላ አንድ ሰላማዊ እንደሆንኩ የሚያውቀኝ መቶ አለቃ ዋስ ሆኖኝ ከእስር ቤት ተለቀቅኩኝ።

ከዚያ በኋላ እዚያ የነበሩኝን ሥራዎች ሳልጨርስ ሳልወድ በግድ አካባቢውን ለቅቄ ወጣሁ።

Image copyright Daawiit Iteefa

ለጥቆም ''የሃምቢሳ እናትና ኑሮዋ'' የተሰኘ ስዕል ሠራሁና ምዕራብ ወለጋ በቢላ ከተማ ውስጥ ሰቀልኩ።

ስዕሉ አንዲት የኦሮሞ እናት የምታሳልፈውን ህይወት ለማሳየት በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራ ነበር።

የሃምቢሳ እናት ደሃ ነች፤ ሃምቢሳ ዛሬም በሕይወት አለ፤ የሃምቢሳ ልጅ አምና እሬቻ ላይ ከሞቱት ውስጥ እንዱ እንደሆነ ሰምቼ በጣም ነበር ያዘንኩት።

ስዕሉ ጸረ-አብዮት ነው ተብሎ ተወሰደና ወደ ሌላ ተላከ፤ ስዕሎችን የምሰራበት ስቱድዮም ታሽጎ እኔንም ለማሰር ሲያፈላልጉኝ አምልጬ የሽሽት ጉዞዬን ወደ ድሬዳዋ አደረግኩኝ።

ከሰባት ዓመት የሽሽት ኑሮ በኋላ መንግሥት በመለወጡ በ1983 እ.አ.አ ወደ ነቀምቴ መጣሁና 'ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች' የሚል ስዕል ሰራሁና በነቀምት ከተማ መሃል ሰቀልኩ።

ይህም ሌላ ስደት አመጣብኝ ስዕሉን አውርደው ካቃጠሉት በኋላ ሠሪውንም እናቃጥላለን ብለው አካባቢው ያለው የፀጥታ ጠባቂዎች እኔን ለመያዝ ፍተሻ ጀመሩ።

እኔም ተደብቄ ከቆየሁ በኋላ ከዚያው በመሸሽ አዲስ አበባ ገባሁ። እዚያም ብዙ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲበዛብኝ ወደ ነገሌ ቦረና ብሄድም ሁኔታዎች ሲብስቡኝ ወደ ኬንያ ተሻገርኩ።

ወደ ኬንያ ከመጣሁበት ቀን ጀምሮ የአዕምሮ እረፍት አገኘሁ፤ ይህ ማለት ችግር አለልደረሰብኝም ማለት አይደለም። ፖሊሶች በየቦታው እያስቆሙ ያስቸግሩኝ ነበር።

እድለኛ ሆኜ ሂደቱ ተፋጥኖልኝ በስተመጨረሻም አውስትራሊያ ገባሁ። ነጻነትና እኩልነት የተረጋገጠበት የሰላም ሀገር በመሆኑና ትልቅ እረፍት በማግኘቴ የወደፊት ህይወቴ ላይ በማተኮር ሥራዬ ላዬ ተጠመድኩኝ።

ከማውቀው ስራ በመነሳት ስዕልና የማስታወቂያ ሥራ ጀመርኩኝ። የምወደውና ተሰጥኦዬ ነው ወደምለው ሙያ እንድመለስና በሁለት እግሬ እንድቆም አደረገኝ።

በመቀጠልም ቤት ገዝቼ አድሼ አሰማምሬ በመሸጥ ገቢ ማግኘት ጀመርኩኝ፤ በዚህም ተሳካልኝ።

ከዚህ በኋላም ከባለቤቴ ጋር በመሆን የአበባ ማሳመሪያና መሸጫ ሱቅ ከፈትን። ባለቤቴም አበቦችን ማሰማመርና አስጊጦ ማቅረብ ስለምትወድ ይህ ስራችንም የተሳካ ሆነልን።

በተለይም በዚህ ሀገር የተለያዩ ወቅቶችን በመከተልና በቀን ተቀን ኑሮ ውስጥ አበባ ምን ያህል ተፈላጊ መሆኑን መገንዘብ መቻላችን ደግሞ ወደ አበባ እርሻ እንድንገባ አደረገን።

ከዚያም 10 ሄክታር የሚያክል መሬት በራሳችን ገንዘብ በመግዛት የዛሬ ሰባት ዓመት የአበባ እርሻ ጀመርን። አሁን በ9 ሄክታር መሬት ላይ የአበባ ማሳደግ ስራ እየሰራን እንገኛለን።

ዘጠኝ ሄክታር በዚህ ሀገር ትንሽ ቦታ ነው። ነገር ግን ጥሩ ጅምርና ለወደፊት ሊያድግ የሚችል መሆኑ ጥርጥር የለውም። የሥራ ዕድልም መፍጠር ችለናል።

Image copyright Daawiit Iteefa

ለእኔ ስኬት ማለት አንድ ሰው በሚሰራው ሥራ መደሰት ማለት ነው፤ በምንሠራቸው ነገሮች ደስተⶉች ነን። ህልማችንም እየተሳካልን ነው ስለዚህ ለእኔ ስኬት ማለት ይህ ነው።

በሕይወቴ ለሆነው ስኬት ሁሉ የአባቴና የእናቴ ድርሻ ከፍተኛ ነው።

በማይመች ሁኔታም ውስጥ በእርሻውም ሆነ በንግዱ ዘርፍ ታላላቅ ጥረቶችን በማድረግ እስከ ጉምሩክ ሱዳን ድረስ እየሄዱ ሲነግዱ እያዩ ከማደግ በላይ ጥንካሬን የሚሰጥና የሚያነሳሳ ነገር የለም።

ሁኔታዎች ቢመቻቹ ወደ ሃገሬ ብሄድና በልማት ሥራ ላይ ብሳተፍ ደስ ይለኝ ነበር ነገር ግን ይህ አሁን የሚመስል ነገር አይደለም። ያ ቀን ግን ቢቆይም እንደሚመጣ አምናለሁ።

በፎቶ የህዝቡን ባህልና ወግ ማንሳትና በሙዚየም አስቀምጦ ለሚመጣ ትልውድ ማስተላለፍ ትልቁ ምኞቴ ነው።

አቶ ዳዊት ኢተፋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት

ተያያዥ ርዕሶች