ኢትዮጵያ ውስጥ የጠፉት ጀርመናዊ ፕሮፌሰር ዱካ አልተገኘም

ፕሮፌሰር ደርክ Image copyright Moritz Loos

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ኢንስቲትዩት ኦፍ አርክቴክቸር ኮንስትራክሽን ኤንድ ሲቲ ዴቨሎፕመንት ወይም በቀድሞ አጠራሩ የህንፃ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪው ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ደርክ ዶናዝ ከጠፉ አንድ ወር ከ17 ቀናቸውን ይዘዋል። አጠፋፋቸው እስካሁን ምስጢራዊ ሲሆን ስላሉበት ሁኔታም ምንም አይነት ፍንጭ አልተገኘም።

ልጃቸው ሞሪትዝ ሉስ ለቢቢሲ እንደገለፁት ከስራ ባልደረቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ኦሞና ማጎ ብሔራዊ ፓርክ በማቅናት ሀገር በቀል የሆነውን የኪነ-ህንፃ ለመመራመር እንዲሁም አካባቢውን ለመጎብኘት እንደሄዱ ይናገራሉ።

በጠፉበት ወቅት በመኪናው ውስጥ አብረዋቸው የነበሩት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የስራ ባልደረባቸውና ጓደኛቸውም በአካባቢው ከስራ በተጨማሪ ለጉብኝትም በተደጋጋሚ አብረው እንደሚሄዱ ይናገራሉ።

መነሻቸውን ያደረጉት በኦሞ ወንዝ አከባቢ ሲሆን በምስራቅ በኩል ኛንጋቶም ቀጥሎም ምጉሉ ወደሚባለው አካባቢ ከዚያም ወደ ደቡባዊ ማጎ ፓርክ በመጓዝ ላይ ነበሩ። "ማጎ ፖርክ ብዙ ቱሪስቶች የሚጎበኙት ስፍራ ሲሆን የሚመጡትም በሰሜን በኩል ነው" በማለት እኚህ ጓደኛቸው ይናገራሉ።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኘው ይህ ፓርክ ከአዲስ አበባ 782 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል። ምንም እንኳን በደቡባዊ የፓርኩ በኩል መግባት ያልተለመደ ቢሆንም ከምጉሉም ወደ ማጎ ፓርክ የሚመጡት በዛው አቅጣጫ ነበር። በመንገዳቸውም ላይ ጥቅጥቅ ወዳለ የደን ቦታ ላይ ደረሱ።

ጓደኛቸው እንደሚናገሩት በዚያው አካባቢ ከሰባት ዓመታት በፊት አልፈው የሚያውቁ ቢሆንም በባለፉት ሶስት ዓመታት ግን መኪና ተነድቶበት እንደማያውቅ ይናገራሉ።

ሞሪትዝ እንደሚሉትም የመኪና ቅያስ መንገድም አልነበረውም። እናም አማራጭ መንገድም ስላልነበር በዚሁ ባልተጠረገ መንገድ ይዘው ጉዟቸውን ቀጠሉ።

በተለይም በጠፉበት ቀን የነበረው የአየር ፀባይ ጭጋጋማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአካባቢውን ሁኔታ ከባድ እንዳደረገውም ጓደኛቸው ይናገራሉ።

መንገዱም ጥቅጥቅ ወዳለ ጫካ ሲጠጋም ያሉበትን ቦታ ማወቅ ስላልቻሉ ፕሮፌሰር ደርክ ከመኪናው በመውረድ አካባቢያቸውን ማሰስ እንደጀመሩ ይኼው ጓደኛቸው ይናገራሉ።

ለአስር ደቂቃዎችም ጥቅጥቅ ወዳለው ጫካ በእግራቸው ገብተው አቅጣጫ ለማመላከት እየሞከሩ ነበር።

ከብዙ ደቂቃዎች በኋላ ግን ባለመመለሳቸው በሁኔታው የተደናገጡት ጓደኞቻቸው የእግር ዱካቸውን በመከተል አሰሳ ጀመሩ።

በአሳዛኝ ሁኔታ ተንቀሳቃሽ ስልክም ሆነ የአቅጣጫ ማመላከቻ (ጂፒኤስ) መኪና ውስጥ ትተው በመሄዳቸው የመኪናቸውን ጥሩንባ በማስጮህ፣ በመጮህ ቢፈልጓቸውም ውጤታማ አልነበሩም። "ደኑ ጥቅጥቅ ያለ በመሆኑ ከሃምሳ ሜትር በላይ ድምፃችን ደኑን ማለፍ እንዲሁም መሰማት አልተቻለም" በማለት ጓደኛቸው ይናገራሉ።

Image copyright Moritz Loos

ይመለሳሉ በሚልም መብራቶቻቸውን አብርተው፤ ዛፎቹም ላይ መብራቶችን ሰቅለው እየጠበቁ አደሩ።

ድንገት ቢመለሱ እንዳያጡዋቸውም በሚል ዛፍ ላይም ተሰቅለው አደሩ። ከዚህም በተጨማሪ የድንገተኛ ሳተላይት ጥሪዎች ለጀርመኑ ድርጅት ጂአይዜድ ተላከ።

የአካባቢው ባለስልጣናት በፍለጋው ላይ የተሳተፉ ሲሆን በቀጣዮቹም ቀናት በቀጣይነትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰራዊት በፍለጋው እንደተሳተፉ ሞሪትዝና ጓደኛቸው ይገልፃሉ።

ከ50-70 የሚሆኑ የሰራዊቱ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ለአስር ቀናትም በተጠናከረ መልኩ አሰሳቸውን ቢቀጥሉም ምንም ፍንጭ እንዳልተገኘ ሞሪትዝና ጓደኛቸው ይናገራሉ።

ሞሪትዝ እንደሚናገሩትም በውሻና በሄሊኮፕተር ለመፈለግ ሙከራ ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸው ይናገራሉ።

ልጆቻቸውና እህታቸውም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሁም ወደ አካባቢው በመሄድ ፈልገዋቸዋል።

"በእያንዳንዱ ጫካና ሰርጥ ብንገፈልግም ልናገኛቸው አልቻልንም" በማለት አቶ ሞሪትዝ ስለ እልህ አስጨራሹ ፍለጋ ይናገራሉ።

አካባቢውን በደንብ እንደሚያውቁት እንዲሁም ለዓመታትም ብዙ አገራትን የመጓጓዝ ልምድ እንዳላቸውም የሚናገሩት ሞሪትዝ በህይወት እንዳሉ ከፍተኛ ተስፋ አላቸው።

"ምናልባት ውሃ ጠምቶት ቅርብ ወደሚገኘው ማጎ ወንዝ ሄዶ ይሆናል፤ በአካባቢው ትንሽ መንደርም አግኝቶ እየኖረ ይሆናል" በማለት ተስፋቸውን ሞሪትዝ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን እያንዳንዷን መንደር መሸፈን ባይችሉም ጠፉበት ከተባለው ቦታ ጀምረው ፎቷቸውን ያሰራጩ ሲሆን ያሉበትን ለሚያውቅም ሆነ ለሚያገኛቸው ሰው 25 ሺ ብር ሽልማት አዘጋጅተዋል።

ጓደኛቸው በበኩላቸው በቀላሉ ኑሮን እንዲሁም አካባቢዎችን መለማመድ የሚችሉ ሰው ስለሆኑ አንድ መንደር ውስጥ እየኖሩ እንደሆኑ ተስፋ ያደርጋሉ።

ፕሮፌሰር ደርክ ማን ናቸው?

የ56 ዓመቱ ዕድሜ ባለፀጋ ፕሮፌሰር ደርክ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ ዘጠኝ ዓመታትን አስቆጥረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ኢንስቲትዩት ኦፍ አርክቴክቸር ኮንስትራክሽን ኤንድ ሲቲ ዴቨሎፕመንት ያስተምሩ ነበር።

ለብዙ ዓመታትም ጀርመን በሚገኘው ባውሃውስ ዩኒቨርስቲም አስተምረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከባውሃስ ዩኒቨርስቲና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር 8000 ያህል አዳዲስ ለሚወጡ የገጠር ከተሞችም ላይ "ኢንተግሬትድ ኢንፍራስትራክቸር" በሚባል ፕሮጀክት ስር የከተማ እንዲሁም የቤቶችን ዕቅድም እየሰሩ ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ቴክኖሎጂን በመጠቀም በቀላሉ የሚሰሩ፣ ውድ ያልሆኑ፣ አካባቢን የማይበክሉ የመገንቢያ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የህንፃ አሰራርን በመመራመርና በመስራትም ላይ ነበሩ።

ይሄም በአዲስ አበባ እየተወደደ ለመጣውና በቤት እጥረት ለሚሰቃየው ህዝብ መፍትሄ ይሰጣል ተብሎ ታምኖበታል።

በሙያቸውም በኪነ-ሕንፃ (አርክቴክቸር)ና በኮምፒውተር ሳይንስ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አላቸው።

ተያያዥ ርዕሶች