በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ኤርትራውያን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ

ኤርትራውያን የተቃውሞ ሰልፈኞች

በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ጥቅምት 21 በኤርትራ የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ በመደገፍ ትላንትና ህዳር 15 በኣፍሪካ ህብረት ፅ/ቤት ሰላማዊ ሰልፍ ኣካሄዱ።

ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ በተለያዩ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች እንዲሁ በተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።

እነዚህ ተቃዋሚዎች "ትምህርት እና ኣምልኮ መሰረታዊ ሰብዓዊ መብት ነው"፤ "የታሰሩ ይፈቱልን"፤ "የኤርትራ ህዝብ ሙስሊም እና ክርስትያኑ አንድ ነን" ፤ "እምቢ ለኣምባገነን"፤ "አዎ ለፍትህ!" የሚሉ መፈክሮች በትግርኛ እና በዓረብኛ ያስተጋቡ ነበር።

መፈክሮቻቸውንም እያሰሙ በከተማዋ ጎዳናዎች ተጉዘው በአፍሪካ ህብረት ግቢ በመሰባሰብ ተቃውሟቸውን በማሰማት ስላካሄዱት አላማ የሚመለከት ፅሁፍ ለኣፍሪካ ህብረት ተወካይ ኣስረክበዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ክልል በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ስፍራዎች "ማይ ዓይኒ"፣ "ሕፃፅ"፣ "ሽመልባ" እና "ዓዲ ሐሩሽ"፤ በዓፋር ክልል ደግሞ "በራሕለ"፣ "አሳይታ" እና በሌሎች ሁለት የስደተኞች መጠለያ ስፍራዎችም የተቃውሞ ሰልፍ ኣካሂደዋል።

በአዲስ አበባ በተካሄደው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ የተሳተፈው ግርማይ የተባለ ኤርትራዊ ስደተኛ "በኤርትራ፡ ዜጎቻችን እየተሰቃዩ ስለሆነ የአክርያ አካባቢ ነዋሪዎች የእስልምና ተከታይ ዜጎቻችንን በሰላም እንዳይማሩ ዕንቅፋት ስለገጠማቸው ወደ አደባበይ ወጥተው ላሰሙት ተቃውሞ ለመደገፍና ድምፄን ለማሰማት ነው የወጣሁት" በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ዓላማችን ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ያሉት የኤርትራ ተወካዮች በኤርትራ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያውቁና እንዲቃወሙ ነው። ወጣቶች በወታደራዊ ግዳጅ፣ በስደትና በእስራት ላይ ስለሚገኙ ከዚህ ችግር እንዲላቀቁ የየበኩላቸውን እንዲወጡ እንፈልጋለን" ብሏል።

ከ ዘጠኝ ዓመታት በፊት የኤርትራ መንግስትን ተቃውሞ ለስደት የበቃው እስክንድር ዘሪሁን በበኩሉ በእስራት ላይ የሚገኙ የ93 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ሸኽ ሙሳን እና ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ በእስር ላይ የሚገኙት ፍትህ እንዲያገኙ እና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው ድምፄን ለማሰማት ነው ሰልፍ ያወጣሁት ብሏል።

ኤርትራ ውስጥ ለሁለት ዓመት ከታሰረች በኃላ አምልጣ የወጣችው ሄለን ገብረአምላክ በበኩሏ " መንግሥት በሃይማኖትና ትምህርት ላይ ጣልቃ በመግባቱ በአስመራ ተቃውሞን ያሰማ ህዝብ ለመደገፍ ነው የወጣሁት" ብላለች።

በኣዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኢማም አቡበከር በበኩላቸው "ህዝባችን በአጠቃላይ ትንሹም ትልቁም እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ይሄ ስቃይና መከራ ይብቃ ለማለት ነው ለተቃዉሞ የወጣሁት" ብለዋል።

በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች በአስመራ የተካሄደውን ተቃውሞ በመደገፍ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ ላይ የተካሄደውን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በተመለከተ በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ መንግስት ተወካዮችን ለማነጋገር በኢሜይልና በስልክ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

ተያያዥ ርዕሶች