በዚምባብዌ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ አራቱ ቁልፍ ግለሰቦች

ከግራ ወደ ቀኝ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ፣ ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ፣ ከምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው የተባረሩት ኤመርሰን ምናንጋግዋ እና ጄነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌጋ Image copyright AFP/Reuters/EPA

የዚምባብዌ ጦር ሃገሪቱን የተቆጣጠርኩት በሙጋቤ ዙሪያ ያሉትን የጦር ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር ለማዋል ነው ማለቱ ይታወሳል።

በዚምባብዌ ፖለቲካዊ ቀውስ መስተዋል የጀመረው ሮበርት ሙጋቤ ምክትላቸው የነበሩትን ኤመርሰን ምናንጋግዋ ከስልጣን በማንሳት በምትካቸው ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤን ሊተኩ ካቀዱ በኋላ ነው።

የሃገሪቱ የጦር አዛዥ ጀነራል ኮስታንቲኖ ቺዌንጋ ባሳለፍነው ሰኞ በዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ውስጥ መከፋፈል ካልቆመ ጦሩ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል አስጠንቅቀውም ነበር።

• የዚምባብዌ ጦር "ጣልቃ እንደሚገባ" አስጠነቀቀ

የፖለቲካ ተንታኞች አሁን ላይ የዓለም ሕዝብ ቀልብን መሳብ በቻለው የዚምባብዌ ፖለቲካ ኡደት ውስጥ አራት ቁልፍ ሰዎች አሉ ይላሉ።

1. ሮበርት ሙጋቤ

Image copyright Reuters

ዚምባብዌ በአውሮፓውያኑ 1980 ነጻነቷን ከቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ከተቀዳጀች በኋላ በተደረገ ምርጫ ነበር አሸንፈው ወደ ስልጣን የመጡት።

ሙጋቤ በስልጣን ዘመናቸው ከከወኗቸው ተግባራት በ1990ዎቹ መባቻ ላይ ያከናወኑት ሁሌም ይወሳል። በወቅቱ ሙጋቤ በጥቂት ነጮች ተይዞ የነበረውን ሰፊ መሬት በመንጠቅ ለጥቁር ዚምባብዌውያን አከፋፈሉ።

ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በሥልጣን የቆዩት የ93 ዓመቱ የእድሜ ባለጸጋ ሙጋቤ ስልጣን ለመልቀቅ ምንም አይነት ፍላጎት ባያሳዩም ጤናቸው ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መምጣቱን ተከትሎ የሚተካቸው ማነው የሚለው ጥያቄ በበርካቶች ዘንድ ነበር።

በተለይም ደግሞ በቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤና በቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት በኤመርሰን ምናንጋግዋ መካከል ውጠረት ተፈጥሮ ቆይቷል።


2. ግሬስ ሙጋቤ

Image copyright Reuters

የሮበርት ሙጋቤ ሁለተኛ ሚስት የሆኑትና ከሙጋቤ በ40 ዓመት የሚያንሱት ግሬስ ሙጋቤ ከፕሬዝዳንቱ የቢሮ ፀሐፊነት በመነሳት በሃገራቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴት ለመሆን በቅተዋል።

ወዳጅና ደጋፊዎቻቸው "የድሆች እናት" እያሉ የሚጠሯቸው ግሬስ በነቃፊዎቻቸው ዘንድ ደግሞ ለሥልጣንና ሃብት እንደሚስገበገቡ ተደርገው ሲሳሉ ይስተዋላል።

የሃገሪቱ ቀዳማዊ እምቤት መሆናቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ ሙጋቤ ላይ የጣሉት የጉዞና ሃብት ማንቀሳቀስ እገዳ ለእርሳቸውም አልቀረላቸውም።

ግሬስ ሃይለኛ ተናጋሪ እንደሆኑም ይነገራል፤ ሙጋቤ ምክትላቸውን ባባረሩበት ወቅት ምናንናግዋ "እባብ ስለሆነ ጭንቅላቱ መመታት አለበት" ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም።


3. ኤመርሰን ምናንናግዋ

Image copyright EPA

ግሬስ ሙጋቤ ብቅ ብቅ ከማለታቸው በፊት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የሙጋቤ 'ትክክለኛ' ምትክ ተደርገው ነበር የሚቆጠሩት።

ከምክትል ፕሬዝደንትነታቸው ከተባረሩ በኋላ ለህይወቴ ያሰጋኛል በማለት ሃገር ጥለው ሸሽተው ነበር።

የልተረጋገጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ግን ጦሩ ሃገሪቱ ከተቆጣጠረ በኋላ ኤመርሰን ምናንጋግዋ ወደ ዚምባብዌ ተመልሰዋል።

በግብፅና በቻይና ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱት ኤመርሰን ላይቤሪያን ከቅኝ ግዛት ለማስወጣት በነበረው ትግል የራሳቸውን ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ ይነገራል።

ከነፃነት በኋላ በነበሩት ዓመታት በተከሰተ ግጭት በርካቶች እንደሞቱ ሲነገር በዚያን ጊዜ የደህንነት ሚኒስቴር የነበሩት ኤመርሰን በደረሰው ጥፋት ውስጥ ምንም ዓይነት ድርሻ የለኝም ብለውም ነበር።

በዚምባቡዌያን ዘንድ 'አዞ' እየተባሉ የሚጠሩት ኤመርሰን የደህንነት ሚኒስቴር ሆነው ከመሥራታቸው አንፃር የሃገሪቱን ጦር ኃይልና የደህንነት ኤጀንሲውን በደንብ እንደሚያውቁት ይነገራል።


4. ጄኔራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ

Image copyright AFP

የምናንጋግዋ ቅርብ ወዳጅ ናቸው የሚባሉት የ61 ዓመቱ ጄኔራል ኮንስታንቲኖ የዚምባብዌን ጦር ኃይል ከአውሮፓውያኑ 1994 ጀምሮ መርተዋል።

በ2002 የአውሮፓ ሕብረት፣ አሜሪካና ኒውዚላንድ የጉዞና የንብረት ማንቀሳቃስ እገዳ ከጣሉባቸው የዚምባብዌ ባለሥልጣናት አንዱ ጄኔራል ኮንስታንቲኖ ነበሩ።

ዕለተ ሰኞ የዚምባብዌ ጦር ኃይል በፖለቲካ ኡደቱ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ግልፅ የሆነ መልእክት ሲያስተላልፉ ብዙዎች እጅግ ተገርመው ነበር።

እርሳቸው ይህን ባሉ በሁለተኛው ቀን የዚምባብዌ ጦር ሃገሪቱን የተቆጣጠሩ ሲሆን መፈንቅለ-መንግሥት አለመሆኑን በቴሌቪዠን ቀርበው ተናግረዋል።

አሁን ላይ ሙጋቤ በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን በቀጣይ ቀናት ምን ሊሆን እንደሚችል በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ