የዳቪንቺ ስዕል ክብረወሰንን ሰብሮ ተሸጠ

Salvator Mundi Image copyright Christie's

500 ዓመታትን እንዳስቆጠረና በሰዓሊ ሊዎናርዶ ዳ ቪንቺ እንደተሳለ የተነገረለት ስዕል በ450 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ተሽጧል።

"የዓለም ጠባቂ" የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ ስዕል በጥበብ ሥራዎች የጨረታ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ገንዘብ ለመሸጥ ችሏል።

በአውሮፓውያኑ 1519 ሕይወቱ እንዳለፈ የሚነገርለት ዳ ቪንቺ "የዓለም ጠባቂ" የተሰኘው ሥራውን በ1505 እንደሠራው ይታመናል።

በ100 ሚሊዮን ዶላር ለጨረታ የቀረበውን የጥበብ ውጤት ማንነቱ ያልታወቅ ግለሰብ ነው በስልክ ድርድር በጠቅላላ ዋጋ 450 ሚሊዮን ዶላር የግል ንብረቱ ማድረግ የቻለው።

Image copyright AFP

ይህ ስዕል በአውሮፓውያኑ 1958 ለንደን በሚገኝ የጨረታ ማስኬጃ ሥፍራ በ45 ዩሮ ተሽጦ ነበር። ነገር ግን የዛኔ ስዕሉ የሌዎናርዶ ሳይሆን የሱ ተማሪ የሆነ ሰው እንደሳለው ተደርጎ ነበር የተሸጠው።

የ19ኛው ክፍለ ዘመን ጥበብ ጥናት ምሁር የሆኑት ዶ/ር ቲም ሃንተር ስዕሉ "የ21ኛው ክፍለ ዘመን አስገራሚ ግኝት" ሲሉ ይጠሩታል።

"ዳ ቪንቺ 20 የሚሆኑ የዘይት ቅብ ያረፈባቸው ስዕሎች ሠርቷል። ከእነዚህ መካከል በጥሩ ይዘት ላይ ያለ መሰል ጥበብ ማግኘት እጅግ አስደናቂ ነው'' ሲሉ ያክላሉ።

ስዕሉ ለጨረታ ከመቅረቡ በፊት በሩስያዊው ቢሊዮነር ዲሚትሪ ሪቦሎቭሌቭ እጅ ነበር የሚገኘው። ቢሊየነሩ ስዕሉን ወርሃ ግንቦት 2013 በ127.5 ሚሊዮን ዶላር ነበር የገዛው።

ምንም እንኳ ስዕሉ ጥገናዎችን ቢያልፍም አሁንም በጥሩ ይዘት ላይ ነው የሚገኘው ሲሉ አጫራቾቹ ይከራከራሉ።

ከዚህ በፊት ከፍተኛ ዋጋ ያለው የጥበብ ሥራ በጃክሰን ፖሎክ የተሰራው 'ቁጥር 17ኤ' የተሰኘው ስዕል ሲሆን ዋጋውም 200 ሚሊዮን ዶላር ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች