''እግሬን ባጣም ትልቁን ነገር አትርፌ ለትንሹ አልጨነቅም''

ፍሬህይወት ዜና ስታነብ Image copyright Firehiwot Tamiru

በ2006 ዓ.ም በመጋቢት መገባደጃ ምሽት ሁለት ሰዓት አካባቢ 13 ሰዎችን ጭኖ ከአዲስ አበባ የተነሳው በተለምዶ 'ዶልፊን' የሚባለው ሚኒባስ ወደ አዳማ እየበረረ ነው።

በዛኑ ቀን ማለዳ ለሥራ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ የሄዱት የፊልም ቀረጻ ቡድን አባላትም ስለቀን ውሏቸው እየተጨዋወቱ የመልስ ጉዞ ላይ ናቸው።

እንደሌሎቹ ሁሉ ፍሬሕይወት ታምሩም ከመሃል መቀመጫ ከመስታወቱ በታቃራኒ ባለው ወንበር ላይ ተቀምጣ አጠገቧ ካለችው የስምንት ወር ነፍሰጡር ጋር እያወራች ነው።

ግን እነዚህ ሁሉ ጨዋታዎች ከሞጆ ከተማ ብዙም አልዘለቁም፤ በቅጽበት ወደለየለት እሪታ ተቀየሩ።

የሚጓዙበት መኪና ወደ አዳማ የሚወስደውን መንገድ ስቶ ከጥቂት ሜትሮች በኋላ ገደል ወዳለበት ቦታ መንደርደር ጀመረ።

በፍጥነት ይጓዝ ስለነበር አሽከርካሪው መኪናውን መቆጣጣር አልቻለም፤ ከጥቂት ጉዞ በኋላ ተገለበጠ።

በእርግጥ ትላለች ከአደጋው ተርፋ ለነጋሪነት የበቃችው ፍሬሕይወት "በአደጋው ብዙዎቹ የደረሰባቸው አደጋ የመፈነካከት፣የመጋጋጥ፤ የመጫጫርና የአጥንት መቀጥቀጥ ጉዳት ነበር።''

እርሷ ግን ከቁርጭምጭሚቷ በታች የደረሰባት አደገኛ ስብራት ከፍተኛ ህመም ፈጥሮባት እንደነበረ ታስታውሳለች።

የተባበሩት መንግሥታት የለፈውን እሁድ የዓለም የትራፊክ ተጎጂዎች ቀን በሚል አስቦት አልፏል።

በአጋጣሚ አደጋው ሲከሰት ከኋላቸው በነበረ መኪና ውስጥ ያሉ ሰዎች ወደ አደጋው ቦታ ቶሎ በመድረሳቸው ተጎጂዎችን ይዘው ወደ አዳማ ሆስፒታል ነጎዱ።

ያኔ ነበር ገና በድንጋጤ ስሜት ላይ እያለች አስደንጋጩን ዜና የሰማችው።

"አዳማ ሆስፒታል እንደደረስኩኝ ሃኪሞቹ ጉዳቴን ከመረመሩ በኋላ አደጋው መጠገን የሚችል ስላልሆነ ከቁርጭምጭሚቴ በታች ያለው የእግሬ ክፍል መቆረጥ እንዳለበት ነገሩኝ ፤እኔ ደግሞ ያኔ አይደለም ስለእግር መቆረጥ ስለህክምናው በትክክል ማሰብ አልቻልኩም ፤ ምክንያቱም በሕይወት መትረፌን አላመንኩም ነበር፤ ካሁን ካሁን የምሞት እየመሰለኝ፣ ሌላ ቦታም ተጎድቼ ይሆን እያልኩ ሰውነቴን ነበር የምፈትሸው'' ትላለች ።

Image copyright Firehiwot Tamiru
አጭር የምስል መግለጫ ፍሬሕይወት ከአደጋው በኋላ በህክምና ላይ እያለች ከጠያቂዎቿ ጋር

ፍሬሕይወት በወቅቱ የቀድሞው የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የአሁኑ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በአማርኛ ለሚያስተላልፈው ዘገባ በሪፖርተርነትና በዜና አንባቢነት ትሰራ ነበር፤ የተለያዩ መድረኮችንም ታዘጋጃለች።

'' የባሰ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበኝ ነው ያሰብኩት ፤እግሬ ብቻ አልመሰለኝም ነበር፤ ከዚያ ሃኪሙን 'እግሬ ብቻ ነው 'አልኩት 'አዎ' ሲለኝ በቃ 'እግሬ ካልጠቀመኝ ቆርጠህ ከላዬ ላይ ጣለው መትረፌ ትልቅ ነገር ነው አልኩት'።''

በእርግጥ ውሳኔው ለፍሬሕይወት ቀላል አልነበረም። ነገር ግን በዛች ቅጽበት እግሯን ለማጣት ከመቃረቧ በላይ 'እኖርላቸዋለሁ' ለምትላቸው ልጆቿ ስትል በሕይወት መትረፏን ነበር እንደተዓምር ያየችው።

"እግዚአበሔር ጠብቆን ነው እንጂ ጥቂት ሸርተት ቢል ቀጥታ ወደገደሉ ነበር የሚገባው፤ የሚገርመው ከጎኔ የነበረችው የስምንት ወር ነፍሰጡር ከእግር መጫጫር የዘለለ አደጋ አልገጠማትም፤ ልጇ ላይ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ከወር በኋላ በሰላም ተገላግላለች።''

ያኔ አደጋው ሲደርስባት የመጀመሪያ ልጇየ6 ፣ሁለተኛው ደግሞ ገና የአንድ ዓመት ህጻን ነበሩ።

Image copyright Firehiwot Tamiru
አጭር የምስል መግለጫ '' ለልጆቼ ጉዳቱን ማስረዳት ከብዶኝ ነበር''

የእርሷ ጉዳት ከሌሎች የባሰበት ምክንያት ከአቀማመጧ ምናልባትም ካደረገችው ጫማ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ታስባለች።

''ረጅም ታኮ ጫማ ነበር ያደረግኩት፤እግሬንም በደንብ ዘርግቼው ከፊት ለፊት ባለው ወንበር ሥር ከትቼው ነበር ፤ ያ ይመስለኛል መኪናው ሲገለባበጥ ቁርጭምጭሚቴ አካባቢ ወንበሩ ይዞኝ የተሰበረው''

እርሷ ከኋላ ስለነበረች አታስተውለው እንጂ ጋቢና የተቀመጡት ተሳፋሪዎች ሹፌሩ ፍጥነቱን እንዲቀንስ ሲነግሩት እንዳንዴም እንቅልፍ ወሰድ ሲያደርገው በጩኸት እየተናገሩ እንደነበር ከአደጋው በኋላ ሰምታለች።

እርሷ ተስፋ በመቁረጥ እግሯ እንዲቆረጥ ብትወስንም ቤተሰቦቿ አይሆንም ብለው በማግስቱ ጠዋት ወደአዲስ አበባ ይዘዋት ሄዱ።

በሙያው ስመጥር የተባሉ ሃኪሞች ጋር ቢወስዷትም የሁሉም መልስ ተመሳሳይ ሲሆን የማይቀረውን እጣ ተጋፈጡ፤ ከቁርጭምጭሚቷ በታች ያለው የእግሯ ክፍል ተቆረጠ።

''ሁልጊዜም ቤተሰብ ሙሉ በመኪና አደጋ አለቀ፤እናት ከልጇ ተነጠለች ሲባል ስለምሰማ ሞት ባይቀርልኝም በመኪና እንዳይሆን እፈራ ነበር፤ደግሞም ጠንቃቃ ነበርኩኝ፤ ጋቢና አልቀመጥም፤ትንሽ ፈጠን ሲል 'እረ ቀስ'እያልኩኝ እጨቃጨቅ ነበር፤ ግን የተጻፈልኝን መኖር ስላለብኝ …''

ፍሬሕይወት ተጻፈልኝ የምትለው እጣፈንታ የእግሯ ክፍል ሲቆረጥ የገጠማትን ለመቋቋም የሚያስቸግር ህመም በድጋሚ እንድታስተናግድ ግድ አላት።

'' መጀመሪያ ከተቆረጠ በኋላ ሌላ ስፔሻላይዝድ ሃኪም መጣና 'በትክክል አልተቆረጠም፤ በኋላ ለሰው ሰራሽ እግርና ለጫማ ያስቸግራታል' አለ፤ ስለዚህ አማራጭ ስላልነበረኝ ድጋሚ ቀዶ ጥገና ተደረገልኝ''

Image copyright Firehiwot Tamiru
አጭር የምስል መግለጫ ''እንዴት መራመድ እንዳለብኝ ከ1ወር በላይ ተማርኩኝ''

አሁን ፍሬሕይወት የገጠማትን አደጋና ያሳጣትን ነገር በየጊዜው እያሰቡ ከማዘን ወጥታ ወደ ቀድሞ ስራዎቿ ተመልሳለች።

''በክራንች እየተንቀሳቀስኩ ቁስሉ ሲደርቅ ሰው ሰራሽ እግር በልኬ ተዘጋጅቶልኝ ከፍታ፣ቁልቁለት፣አዳላጭ መንገድን እንዴት መራመድ እንዳለብኝ ከ1ወር በላይ ተማርኩና በሂደት ወደ ዘገባና መድረክ ዝግጅት ተመለስኩኝ። አሁን በፊት የምሰራውን ሁሉ እሰራለሁ፤ የቀረብኝ ነገር ቢኖር በፊት የሞዴሊንግ ስራ እሰራ ነበር አሁን አልሰራም። ትልቁን ነገር አትርፌ ለትንሹ መጨነቅ አልፈልግም''