የዓለምን የንግድ እንቅስቃሴ ያዘመኑት የብረት ሳጥኖች

ኮንቴይነሮች Image copyright Getty Images

በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ የንግድ ግብይቶች ከዓለም የኢኮኖሚ ውጤቶች ወይም ከሀገር ውስጥ ምርት ከሚገኘው ገቢ ከ20 በመቶ በታች የሚሆነውን ብቻ ነበር የሚሸፍኑት።

አሁን ግን ድርሻቸው ወደ 50 በመቶ ገደማ ደርሷል፤ ነገር ግን በዚህ ሁሉም ሰው ደስተኛ አይደለም።

በንግድ ዙሪያ የሚካሄዱት ክርክሮች ድንበር የለሹን የንግድ ግንኙነትን(ሉላዊነትን) በንግድ ስምምነቶች የሚመራ ፖሊሲና ርዕዮተ ዓለም አድርገው ያስቀምጡታል።

ሆኖም የሉላዊነት ትልቁ አንቀሳቃሽ ነጻ የንግድ ስምምነቶች ሳይሆኑ ቀላሉ የማጓጓዣ ኮንቴይነሮች ፈጠራ ሊሆን ይችላል።

በእርግጥ 2.4 ሜትር ስፋት፣ 2.6 ሜትር ከፍታና 12 ሜትር ርዝመት ያለው አነስተኛ የብረት ሳጥን ሊሆን ይችላል፤ ተጽዕኖው ግን ከዚህ በእጅጉ የገዘፈ ነው።

አሮጌው መንገድ

በአውሮፓውያኑ 1954 የዕቃ ጫኝ ማጓጓዣ መርከብ 'ኤስ ኤስ ዋርየር' ከኒውዮርክ ወደ ጀርመን ብሪመርሄቨን ተጓዘ።

መርከቡ 5,000 ቶን የሚመዝኑ ምግቦችን፣ የቤት ውስጥ ዕቃዎችን፣ ደብዳቤዎችንና መኪኖችን ነበር የጫነው።

194,582 አይነት ጭነቶች በተለያዩ 1,156 ማጓጓዣዎች ተጫኑ።

ነገር ግን በወቅቱ ከምንም በላይ አስቸጋሪ የነበረው ዕቃዎቹን በወደብ መጋዘኖች ማራገፉ ነበር።

ተሸካሚዎች ዕቃዎቹን ከመርከቡ እያወረዱ ዝርግና ሰፋ ያለ እንጨት ላይ ያራግፉታል።

እንጨቱም በዚህ መልኩ በዛ ያለ ዕቃ ተጭኖበት በአግባቡ ከተደረደረ በኋላ በገመድ ተንጠልጥሎ በጉተታ ወደተዘጋጀለት ቦታ ይዘዋወራል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ጎታችና ተሸካሚ ተሽከርካሪዎች ቢኖሩም አብዛኛው ዕቃ የሚዘዋወረው በሰዎች ጉልበት ነበር

ይህ ሥራ በጣም አደገኛ ነበር።

በትልልቅ ወደቦች በሳምንታት ውስጥ ሰዎች ይሞቱ ነበር።

በ''ኤስኤስ ዋርየር'' ጉዞ ላይ ጥናት ያካሄዱ ባለሞያዎች እንደሚሉት የጫነውን ዕቃ እስኪያራግፍና እስኪጭን 10 ቀናትን ፈጅቷል።

ይህ ደግሞ ዕቃውን በአትላንቲክ ውቅያኖስ ለማጓጓዝ ከፈጀው ጊዜ ጋር እኩል ነው።

በዚህ ዘመን ዋጋ ሲተመን ዕቃውን ለማጓጓዝ የወጣው ወጪ በአንድ ቶን እስከ 420 ዶላር የሚያስወጣ ነው።

ዕቃውን የማሰራጨትና የመለየት ሂደቱ ከሚወስደው ጊዜ ጋር ሲደመር ሙሉ ጉዞው እስከ ሶስት ወራት ጊዜ ሊወስድ ይችላል።

እናም የተሻለ መንገድ ሊኖር እንደሚገባ ግልጽ ነበር።

የተደበቀ ፍላጎት

የተሻለው መንገድ ሁሉንም ዕቃዎች በትላልቅ ሳጥኖች አድርጎ ማንቀሳቀሱ ሆነ።

የማጓጓዣ ኮንቴይነሮች አስቀድሞም በተለያየ መልኩ ሙከራ ይደረግባቸው ስለነበረ ሳጥኑን መሥራት ቀላል ነበር።

ከዚህ ይልቅ አስቸጋሪ የነበረው ድርጅታዊ እንቅፋቶችን ማለፉ ነበር ።

በመጀመሪያ በሳጥኑ መደበኛ መጠን ላይ የዕቃ ጫኝና የማጓጓዣ ኩባንያዎች እንዲሁም የወደብ አስተዳዳሪዎች መስማማት አልቻሉም።

ይባስ ብሎ ደግሞ የአሜሪካ ተቆጣጣሪ አካልና የወደብ ሰራተኞች ማህበር ሃሳቡን ሳይቀበሉት ቀሩ።

Image copyright MAERSK
አጭር የምስል መግለጫ ማልኮም ማክ ሊን

ዕድሉን መለየት

እነዚህን አለመግባባቶች ለይቶ ዘመናዊውን የማጓጓዣ ኮንቴይነሮች የፈጠረው ሰው ማልኮም ማክ ሊን ይባላል።

ማክ ሊን ስለጭነት መኪና ፈጠራ እንጂ ስለወደብ ማጓጓዣ እውቀት አልነበረውም።

እናም በመጀመሪያ የነበረውን የህግ ክፍተት የማጓጓዣና የጭነት መኪና ኩባንያዎችን ለመቆጣጠር ተጠቀመበት።

የወደብ ሰራተኞች አድማ ሲመቱ እርሱ ያንን ጊዜ የቀድሞ ማጓጓዣዎችን በአዲስ ቀመር ለማዘጋጀት አዋለው።

ሆኖም ዋነው አብዮት የተካሄደው በ1960ዎቹ መጨረሻ ማልኮም ማክ ሊን የማጓጓዣ ኮንቴይነር ሃሳብን ለአሜሪካ ጦር በሸጠበት ጊዜ ነው።

የጦርነት ጥቃት

ዕቃዎችን ወደቬትናም ለማጓጓዝ የተቸገረው የአሜሪካ ጦር የማክ ሊንን ሃሳብ ለመተግበር ወሰነ።

ኮንቴይነሮቹን የተቀናጀ የአቅርቦት ስርዓት አካል በማድረግ በጣም በተሻለ ሁኔታ መጠቀም ይቻላል፤ ለአሜሪካ ጦርም ይህንን ለመተግበር ጥሩ ጊዜ ሆነ።

ከዚህ በተሻለ ማክ ሊን ከቬትናም የመልስ ጉዞ ሲደረግ ባዶ የነበሩት ኮንቴይነሮች ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ከነበረችው ጃፓን ዕቃዎችን ለማጓጓዝ ሊጠቀምባቸው እንደሚችል አሰበ።

የትራንስ-ፓሲፊክ የንግድ ልውውጥም ተጧጧፈ።

Image copyright Getty Images

አዲሱ መንገድ

ዘመናዊ የኮንቴይነሮች መርከብ ከ'ኤስኤስ ዋርየር' በ20 እጥፍ የሚበልጡ ዕቃዎችን ከማጓጓዙም በላይ ለማራገፍ የሚፈጅበት የተወሰኑ ሰዓታት ብቻ ነው።

ግዙፍና እያንዳንዳቸው 1,000 ቶን የሚመዘኑ 'ክሬኖች' 30 ቶን ያህል ከሚከብዱት ተሸካሚ ኪንቴይነሮች ጋር ታስረው በማዟዟር ለሚጠብቃቸው አጓጓዥ ያስረክባሉ።

ሂደቱ ደግሞ የእያንዳንዱን ኮንቴይነር እንቃስቃሴ በዓለማቀፍ ስርዓት ውስጥ በሚቆጣጠሩ ኮምፒዩተሮች ይመራል።

ወጪ የሌለበት ማጓጓዣ?

በእርግጥ የኮንቴይነር አብዮት ሁሉም ቦታ ጥቅም ላይ አልዋለም።።

ሆኖም በየጊዜው ተደራሽነቱን እያሳደገ እንዲሁም ዕቃዎችን በአስተማማኝ መልኩ፣ በአጭር ጊዜና በረከሰ ዋጋ እያጓጓዘ ነው።

በአውሮፓውያኑ 1954 በ''ኤስኤስ ዋርየር'' በአትላንቲክ በኩል አንድ ቶን ዕቃ ለማጓጓዝ ሲወጣ የነበረው የ420 ዶላር ወጪ አሁን ከ50 ዶላር በታች ሊሆን ይችላል።

በዓለማቀፍ ንግድ ላይ ጥናት ያካሄዱ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የማጓጓዣ ወጪ ወደዜሮ ሊጠጋ ይገባል ይላሉ።

የሂሳብ ቀመሩን ያቀለዋል ባይ ናቸው፤ ለማጓጓዣ ኮንቴይነሮች ምስጋና ይግባና ይህ እውነት ለመሆን እየተቃረበ ነው።