ጦሩ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ሙጋቤ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ታዩ

ሙጋቤ በተማሪዎች የምረቃት ፕሮግራም ላይ Image copyright @ZimMediaReview
አጭር የምስል መግለጫ ሙጋቤ በተማሪዎች የምረቃት ፕሮግራም ላይ

የሃገሪቱ ጦር ከሶስት ቀናት በፊት ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ሮበርት ሙጋቤ በአደባባይ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የታዩት።

በዚምባብዌ መዲና በሆነችው ሃራሬ በተማሪዎች የምረቃት ፕሮግራም ላይ ለህዝብ የታዩት።

ላለፉት ጥቂት ቀናት ሙጋቤ በቁም እስር ላይ መቆየታቸው ይታወቃል።

አርብ ጠዋት የዚምባብዌው ሄራልድ ጋዜጣ ሙጋቤ የጦሩን መሪ ጀነራል ኮንስታኒቲኖ ቺዌንጋንና የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ(ሳድክ) ተወካዮች ጋር በቤተመንግሥት ሲነጋግሩ የሚያሳዩ ፎቶዎችን አውጥቶ ነበር።

ሙጋቤ ከሥልጣን አልወርድም እያሉ ነው

ሬውተርስ የዓይን እማኝን ጠቅሶ እንደዘገበው ሙጋቤ በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ ንግግር ካደረጉ በኋላ ከተመራቂዎች ሞቅ ያለ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

ብሔራዊ መዝሙር እየተዘመረ ሙጋቤ በቀይ ምንጣፍ ላይ በዝግታ እየተራመዱ ወደ መድረኩ ሲወጡ ሞቅ ያለ ድጋፍ እና ጭብጨባ ሲደረግላቸው ነበር ሲል የቢቢሲው ሪፖርተር አንድሪው ሃርዲንግ ከሃራሬ ዘግቧል።

የሙጋቤ ባለቤት ግሬስ ሙጋቤም ሆኑ የትምህርት ሚንስትሩ በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ አልተገኙም።

ሙጋቤ በየዓመቱ በዚህ የምርቃት ፕሮግራም ላይ መገኘትን ልምድ ያደረጉ ቢሆንም በቁም እስር ላይ እንደመቆየታቸው በፕሮግራሙ ላይ ይገኛሉ ተብሎ አልተጠበቀም ነበር።

ሙጋቤ እስከቀጣዩ ምርጫ ሥልጣኔን አልለቅም ማለታቸውን የመረጃ ምንጮች እየገለጹ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ