ካለሁበት 10፡ የምመኘው በአንድነታችን ተዋደንና ተከባብረን በኢትዮጵያዊነታችን እንድንኖር ነው

Image copyright FEKADU KEBEDE
አጭር የምስል መግለጫ ዶር ፍቃዱ ከበደ በሥራ ገባታ ላይ

ስሜ ፍቃዱ ከበደ ይባላል አሁን ወዳለሁባት ከተማ ከመምጣቴ በፊት ለ14 ዓመታት ያህል ተሰድጄ በመጣሁባት በፊንላንዷ ሄልሲንኪ ከተማ እኖር ነበር።

በዩክሬን ክሪም በተሰኘው የሕክምና ተቋም የሕክምና ሳይንስ ብማርም የትምህርት ማስረጃዬ በፊንላንድ ሕጋዊ እንዲሆን ያደረኩትም ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላ ነበር።

ከዚያም ለልጆቻችን የተሻለ የትምህርትም ሆነ ማሕበራዊ ኑሮ በማለት ለ14 ዓመታት የኖርንባትን ፊንላንድን ለቀን ወደ ስትክሆልም አመራን።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የስዊድን ታዋቂው 'ጋምላ ስታን' የተሰኘው ወደብ

ብዙውን የአዋቂነት ዘመኔን ማለትም 27 ዓመታት ያክል ከኢትዮጵያ ውጪ ብኖርም ማንኛውም ሰው የተወለድሁበትን ሥፍራ ምን ጊዜም አልረሳውም።

ምንም እንኳ አሁን የምኖርባት ስዊድንና ኢትዮጵያ በርካታ ልዩነቶች እንደሚኖራቸው በብረዳም እጅግ የተሟላው የስዊድን መሠረተ ልማትን ሃገሬ ላይ ባየው ብዬ እመኛለሁ።

ለኔም ሆነ ለቤተሰቤን ፍላጎት የሚያሟላና ሕይወት እጅግ ቀላል የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች የተሟሉላት ሃገር ነች ስዊድን። ምሳሌ ለመጥቀስ እስከ አምስት ሳምንታት ያህል የዓመት ዕረፍት ማግኘት የሚቻልባት ሃገር ናት ስዊድን። አልፎም በወሊድ ወቅት ለእናትም ሀነ ለአባት እኩል የስድስት ወር የእረፍት ጊዜ ይሰጣል።

ቢያስፈልግ አባት ከራሱ ላይ ሶስቱን ወራት ቀንሶ ለባለቤቱ መስጠት ይችላል። እርግጥ የኑሮ ዘይቤው ለየት ማለቱ አንዳንድ ጉዳቶች ሊኖሩት ቢችሉም በብዙ ረገድ ግን ሕይወትን ቀለል ለማድረግ ታስቦ የተዘረጋ በመሆኑ ደስተኛ ያደርጋል።

Image copyright FEKADU KEBEDE
አጭር የምስል መግለጫ '' እንጀራ በየቀኑ ብበላ አይሰለቸኝም''

ከኢትዮጵያ ከወጣሁበት ጊዜ አንስቶ በየዕለቱ እንጀራ ብመገብ አይሰለቸኝም። ዓመት በዓላትን እየጠበቅን ብቻ ሳይሆን በየጊዜው እንጀራና ወጣወጦችን እንመገባለን።

ከጠጥቂት ዓመታት በፊት እንጀራም ሆነ መሰል የምግብ ዓይነቶች ከኢትዮጵያ ነበር የሚመጡት፤ ሊያውም በውድ ዋጋ። አሁን ግን እዚህ ስቶክሆልም ከተማ ኢትዮጵያውያን የሚያስተዳድሯቸው የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች ውስጥ ታሽጎ የሚሸጥ ቁሌት፣ የወጥ ዓይነት፣ በርበሬና እንጀራ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። እንደውም ውድድሩ እየበረታ ሲመጣ ዋጋውም እየረከሰ ነው።

ነገር ግን የኑሮ ዘይቤው ለየት ያለ በመሆኑ በፈለግኩት ሰዓት እንጀራ ላላገኝ እችላለሁ።

እንጀራ ጎድሎብኝ ባያውቅ እንኳ ሀገሬን በጣም እናፍቃለሁ። በተለይ ደግሞ ከቤተሰብ ጋር በፋሲካ በዓል እንደመሰባሰብ የሚናፍቀኝ ነገር የለም።

Image copyright FEKADU KEBEDE
አጭር የምስል መግለጫ ዶሮ በሩዝ ከሰላጣ ጋር

ስቶክሆልም ለየት ያለች ከተማ ናት። በተለይ በመሥሪያ ቤትም ሆነ በትምህርት ቤት የተዘጋጀ ምግብ ማግኘት እጅግ ቀላል ነው፤ ሊያውም በነፃ። ልጆች ቁርስ፣ ምሳና መክሰስ ምን ይበላሉ ወይም ምን ይቋጠርላቸው ብሎ ማንም ሃሳብ ውስጥ አይገባም።

እኔ በተፈጥሮዬ ቁርስ አልበላም። ጠዋት ቡና ካገኘሁ ምግብ አያስፈልገኝም። በተለይ ሥራ ከበዛብኝ ምንም ነገር ላልበላ እችላለሁ። ነገር ግን በመሥሪያ ቤቴ ከሚቀርቡልኝ መካከል ሩዝ በዶሮ ወይንም በዓሣ ከሰላጣ ጋር መብላት እወዳለሁ።

አንደው ሆን ብዬ መስኮት አካባቢ ተቀምጬ ትካዜ ውስጥ ባልገባም ቤታችን ከፍታ ላይ በመሆኑ ደስ የሚል እይታን ይጋብዛል። ጠዋት ጠዋት ልጆቻችን ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ዙሪያ ገባውን ለመቃኘት በመስኮት እቃርማለሁ።

Image copyright FEKADU KEBEDE
አጭር የምስል መግለጫ በመስኮቴ ያለው እይታ

ከሁሉም በላይ በሕይወቴ ደስተኛ ያደረጉኝን ሁለት ነገሮች ያየሁት በስዊድን ነው። ለዚህም ለስዊድን ትልቅ ቦታ አለኝ። የመጀመሪያው ነገር ልጃችን 18 ዓመት ሞልቷት የጥርስ ሐኪም ልትሆን መንገድ ላይ መሆኗ ሲሆን ሁለተኛው ግን አሳዛኝ ክስተትን ያዘለ ነው።

በመሥሪያ ቤት እያለሁ ነበር አስደንጋጭ የስልክ ጥሪ የደረስኝ። የአምስት ወር ገደማ ነብሰ-ጡር የነበረችው ባለቤቴ በመሬት ውስጥ መተላለፊያ መኪና እያሽከረከረች ሳለ ከየት መጣ ሳይባል አንደ ከባድ መኪና አደጋ እንዳደረሰባት ከስልኩ ወዲያኛው ጫፍ ሰማሁ።

የትኛው መንገድ ላይ ትገጭ፣ ምን ጉዳት ይድረስባት፣ ምን ያህል ትጎዳ፣ ፅንሱ ይትረፍ አይትረፍ የማውቀው ነገር አልነበረም፤ ግን ወደተባልኩት ሆስፒታል በፍጥነት አመራሁ። ነገር ግን ባለቤቴም ልጃችንም ጤናማ ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም ነበር።ከባድ መኪናው ውሰጥ የነበሩት አነስተኛ ጉዳት ቢደርስባቸውም እንኳ ያንኑ ዕለት ማታ እጅ ለእጅ ተያይዘን በእግራችን ቤት ገባን። ይኸው ልጃችን በሰላም ከተወለደች ወርሃ ኅዳር ድፍን 11 ዓመት።

Image copyright FEKADU KEBEDE

ኢትዮጵያን የሚያስታውሱኝ ነገሮች እየደበዘዙ ቢሆንም በየሳምንቱ ወደ ቤተ-ክርስቲያን ባቀናሁ ቁጥር ግን ኢትዮጵያ የተመለስኩ ያህል ይሰማኛል። ያለው ስሜት እኔና ባለቤቴን ወደ ሀገር ቤት ሲመልስ ልጆቻችንን ያላደጉባትን ሀገር ያስታውሳቸዋል።

ከቅዳሴ በኃላ በሚዘጋጀው የቁርስ ሥነ-ሥርዓት ልጆች ዳቦ በሻይ እየነከሩ ሲመገቡ ስመለከት ልጅነቴ ትውስ ይለኛል።

አንዳንዴ ባለው ሁኔታ አዝናለሁ። ምክንያቱም እዚህ ስዊድን እንዳለን የቁጥር ብዛት የተደራጀ ማሕበረሰብ የለንም። እንደ አረቦች ባይሆን እንኳ እዚህ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እጅግ ላቅ ያለ ነው። እጅግ ከልቤ የምመኘው በኢትዮጵያዊ አንድነታችን ተዋደንና ተከባብረን እንድንኖር ነው።

ወደ ድሮው መመልስ ብችል ደስ ይለኛል። በተለይ 8 ዓመት ወደተማርኩበት፤ ጌጃ ሰፈር ወደሚገኘው የመሠረተ ሕይወት ትምህርት-ቤት። አሁን ለደረስኩበት ደረጃ መሠረቴ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። መምህራኖቼና ተማሪዎች በእግዚያብሔር እርዳታ ትክክለኛውን የሕይወትን መንገድ እንድከተልና ትምህርቴ ላይ እንዳተኩር ረድተውኛልና።

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገራት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦

ካለሁበት 11፡ በእንግሊዝ ሃገር ትልቁ ችግር ብቸኝነት ነው

ካለሁበት 12፡ ''የአውደ ዓመት ግርግር ሁልጊዜ ይናፍቀኛል''