በሞሮኮ የምግብ እርዳታ ለመቀበል የወጡ 15 ሰዎች ተረጋግጠው ሞቱ

ሞሮኮ አምቡላንስ Image copyright ABDELHAK SENNA

በሞሮኮ የምግብ እርዳታ ለመቀበል በወጡ ሰዎች መካከል በተፈጠረ ግርግር እስካሁን 15 ሰዎች መሞታቸውና በርካቶች መጎዳታቸው ተዘግቧል።

በሞሮኮ ኢሳወይራ በተባለ ግዛት የተፈጠረው ግርግር በአንድ እርዳታ ሰጭ ድርጅት የምግብ እርዳታ ዝግጅት ላይ የተነሳ መሆኑ ታውቋል።

በግርግሩ 40 ሰዎች ያህል ጉዳት እንደደረሰባቸው ሲታወቅ የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ከተጎጂዎቹ መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች እና አዛውንት እንደሆኑ ዘግቧል።

በግርግሩ ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈ ሴቶች መሬት ላይ ተዘርረው የሚያሳዩ ፎቶዎች በማሕበራዊ ሚዲያ ተንሰራፍተው ታይተዋል።

8 ሺህ ሰዎች ገደማ በሚኖሩበት አካባቢ የሚከበረው ዓመታዊው የምግብ እርዳታ ፕሮግራም ብዙ ጊዜ የተወሰኑ ሰዎች የሚካፈሉበት ቢሆንም በዚህ ዓመት ግን ከታሰበው ሰው በላይ መገኘቱንም መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

"ሰዎች እርስ በርስ መገፋፋት ጀመሩ፤ መከላከያ አጥሩንም ጥሰው ገቡ" ሲል አንድ ግለሰብ ለኤ ኤፍ ፒ ዜና ወኪል ተናግሯል። ብዙዎቹ ተጎጂዎች ወደ መዲናዋ ማራካሽ ለሕክምና መወሰዳቸውንም ጨምሮ አስታውቋል።

የሞሮኮ የሃገር ውስጥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እንዳስታወቀው ንጉስ ሙሃመድ 6ኛ የመንደሪቱ ባለስልጣናት የተጎዱትን እንዲያግዙ አዘው፤ የሁሉንም ተጎጂዎች የሕክምና እንዲሁም የሟቾችን የቀብር ወጪ ከግል ኪሳቸው እንደሚሸፍኑ ተናግረዋል።

ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ ተንቀሳቃሽ ምስል እጅግ በርካታ ሰዎች ከግግሩ በፊት በአንድ የገበያ ሥፍራ ተሳብሰበው የምግብ እርዳታ ሲጠብቁ ያሳያል።

ግርግሩ በምን ምከንያት ሊቀሰቀስ እንደቻለ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ተያያዥ ርዕሶች