44 ሰዎችን የያዘው የአርጀንቲና ሰርጓጅ መርከብ ደብዛው ጠፍቷል

The vessel is the newest of the three submarines in the Argentine navy's fleet Image copyright EPA

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ነበር 44 ሰዎችን ይዞ የጠፋው የአርጀንቲና ሰርጓጅ ባሕር ኃይል መርከብ የት ይግባ የት ሳይታወቅ ደብዛው የጠፋው።

ከሰርጓጅ መርከቡ ጋር ግንኙነት ከተቋረጠ በኋላ ፍለጋው ቢቀጥልም እስካሁን ምንም ዓይነት ፍንጭ ሊገኝ እንዳልተቻለም ታወቋል።

ሃገራት አሳሽ ባሕር ኃይሎቻቸውን በመላክ ለአርጀንቲና አጋርነታቸውን ሲያሳዩ አሜሪካ እጅግ ዘመናዊ የሆነውን መርከብ በመላክ ፍለጋውን ተቀላቅላለች።

የባሕር ኃይል ሰርጓጅ መርከቡ ከአርጀንቲና ወደብ 430 ኪሎሜትር ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ መሃል ከገባ በኋላ ነው ደብዛው የጠፋው።

ቅዳሜ ዕለት ቫልዴዝ ሰርጥ አካባቢ ምልክቶች መታየታቸውን ተከትሎ የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ ወደ ቦታው አውሮፕላን ቢልክም ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል።

የሃገሪቱ አየር ኃይል ሰኞ ዕለት በአሰሳው ወቅት ተሰምቶ የነበረው ድምፅ ከጠፋው ሰርጓጅ መርከብ የወጣ እንዳልሆነ አስታውቋል። አሁድ ዕለትም መሰል ምልክት ታይቶ የነበረ ቢሆንም ከጠፋው ሰርጓጅ መርከብ እንዳልሆነ ግን ለማወቅ ተችሏል።

Image copyright AFP

የአርጀንቲና ባሕር ኃይል ሰርጓጅ መርከቡ ቢያንስ ለሁለት ሳምንታት የሚሆን ኦክሲጂን፣ ምግብ እንዲሁም ውሃ ይዞ እንደተንቀሳቀሰ አሳውቋል።

ሰርጓጅ መርከቡ ከደቡብ አሜሪካ ደቡባዊ ጫፍ ተልዕኮውን ጨርሶ በደቡብ ቦነስ አይረስ ወደ ሚገኘው ጣቢያው እየተመለሰ እንደነበርም ሊታወቅ ችሏል። ከዋናው ባሕር ኃይል ጋር ግንኙነቱ የተቋረጠው ባሳለፈነው ሳምንት ረቡዕ ጠዋት ነበር።

የአርጀንቲና ባሕር ኃይልና ሌሎች አጋር አሳሾች ፍለጋቸውን ቢያጧጡፉትም እስካሁን ምንም ዓይነት ፍንጭ ሊገኝ አልቻለም።

ምናልባት በኃይል መቋረጥ ምክንያት ሰርጓጅ መርከቡ ከዋናው ጣቢያ ጋር ግንኘነቱ ሊቋረጥ እንደቻለ ግምቶች አሉ። ነገር ግን ግንኙነት ቢቋረጥም መርከቡ አቅራቢያው ወደሚገኝ የብስ መሄድ እንደነበረበት ደግሞ እየተነገረ ይገኛል።

ከጠፉት 44 ሰዎች መካከል የአንዱ ወንድም የሆነ ግለሰብ ለመጨረሻ ጊዜ ከወንድሙ ጋር በነበረው ግንኙነት ሰርጓጅ መርከቡ ከባትሪ ጋር በተያያዘ ችግር እንደገጠመው መስማቱን ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አሳውቋል።

ነገር ግን የአርጅንቲና ባሕር ኃይል ካፕቴይን ጋሌዚ እንደሚሉት መካኒካዊ ችግር ሁሌም የሚፈጠር እንጂ አዲስ ነገር አይደለም፤ የሚያደርሰው አደጋም እጅግ ዝቅተኛ ነው።

ከአሜሪካ ወደ አርጀንቲና ፍለጋውን ለማገዝ የመጣው ዘመናዊ የውሃ ውስጥ አሳሽ መሣሪያም ፍለጋው ቢቀላቀልም ከባድ የአየር ሁኔታ አሰሳውን እንዳከበደው እየተነገረ ይገኛል።

"ከስድስት እስከ ስምንት ሜትር ርዝማኔ ያለው ማዕበል ፍለጋችንን እጅግ አክብዶብናል" ሲሉ የባሕር ኋይል አድሚራል ባግርኤል ጎንዛሌዝ እሁድ ዕለት ተናግረዋል። "አለመታደል ሆኖ ይህ የአየር ሁኔታ ለሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ይቆያል" ሲሉም አክለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች