ሙጋቤ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ጫና ቢደረግባቸውም በሰጡት መግለጫ 'ስልጣን አለቅም' ብለዋል

ሙጋቤ በቴሌቪዥን መግለጫ ሲሰጡ

ሮበርት ሙጋቤ ከፕሬዝዳንትነታቸው በራሳቸው ፍቃድ እንዲወርዱ ጫና ቢደረግባቸውም ትናንት በሰጡት መግለጫ ስልጣን እንደማይለቁ አሳውቀዋል።

ዚምባብዌ እንዴት ሰነበተች?

በቴሌቪዥን መስኮት ቀጥታ ስርጭት በተላለፈው መግለጫቸው ሥልጣን እንደማይለቁና በቀጣይ ታኅሳስ ወር በሚደረገው የፓርቲው አጠቃላይ ስብሰባ ፓርቲያቸውን በመምራት እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ትናትን ዛኑፒኤፍ ፓርቲ ሮበርት ሙጋቤን ከፓርቲ መሪነታቸው በማንሳት የፕሬዝዳንትነት ሥልጣናቸውን እንዲለቁ እስከ ሰኞ 7 ሰዓት ቀነ ገደብ አስቀምጦላቸዋል፡፡

በፓርቲው በሙጋቤ ምትክ ከሁለት ሳምንታት በፊት በሙጋቤ የተባረሩትን የቀድሞው የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋን የፓርቲው መሪ አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡ ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤን ደግሞ ከአባልነት አባሯል፡፡

ትናንት ምሽት በሃራሬ በርካቶች ሙጋቤ ስልጣን ይለቃሉ በሚል ስሜት ነበር የቀጥታ የቴሌቪዥን መግለጫቸውን የተመለከቱት። በንግግራቸው መጨረሻ ላይ ግን ሙጋቤ ''ከጥቂት ወራት በኋላ በሚደረገው አጠቃላይ ስበሰባ የፓርቲው (ዛኑ ፒኤፍ) መሪ በመሆን እገኛለው'' ሲሉ ተደምጠዋል።

''የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እንደመሆኔ መጠን የጦሩ አባላት የወሰዱት እርምጃ እና የፓርቲው አባላት ስጋት ይገባኛል። ሆኖም ዚምባብዌ ወደ ቀድሞ መረጋጋቷ መመለስ ይኖርባታል'' ብለዋል።

በመግለጫቸው የጦሩ እና የዛኑ ፒኤፍ አባላት ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ስላሳደሩባቸው ጫና ምንም ያሉት ነገር ባይኖርም ጦሩ ስልጣን ተቆጣጥሮ እሳቸውን በቁም እስር ላይ ማዋሉ ጥፋት አይደለም ብለዋል።

ከፓርቲ አባልነታቸው ስለተባረሩት ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ ግን ያሉት ነገር የለም።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ