በጀርባቸው የሚተኙ ነፍሰጡሮች ልጃቸው ሞቶ የመወለድን ዕድል በእጥፍ ይጨምራሉ

ሴቶች በእርግዝናቸው ወቅት በጎን ሊተኙ ይገባል Image copyright Natalie Behring

ሴቶች በመጨረሻ እርግዝናቸው ሶስት ወራት ፅንሱ ሞቶ እንዳይወለድ በጎን በኩል መተኛት እንዳለባቸው አዳዲስ ጥናቶች እያሳዩ ነው።

በአንድ ሺ እርጉዞች በመጨረሻ እርግዝናቸው ወቅት በተደረገ ጥናት በጀርባቸው መተኛታቸው ፅንሱ ሞቶ የመወለዱን አደጋ እጥፍ እንደሆነ ያሳያሉ።

ይህ ጥናትም 291 ሞተው የተወለዱ ፅንሶችንና 735 በህይወት የተወለዱ ፅንሶች ላይ ምርምር አድርጓል።

ተመራማሪዎቹ የእርጉዝ ሴቶች አተኛኝ ለፅንሳቸው ደህንነት በጣም ጠቃሚ እንደሆነና ድንገት ሲነቁም በጀርባቸው ተኝተው ራሳቸውን ቢያገኙትም መጨነቅ እንደሌለባቸውም ይገልፃሉ።

ይህ በእንግሊዝ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ከ225 እርግዝናዎች ውስጥ አንደኛው ፅንስ እንደሚሞትና ሴቶች በጎን በኩል ቢተኙ 130 የሚሆኑ ፅንሶች በየዓመቱ በህይወት መወለድ ይችሉ ነበር ይላል።

ብሪትሽ ጆርናል ኦፍ ኦብስተትሪክስና እና ጋይናኮሎጂ በሚማል ጆርናል የታተመው ይህ ሚነስ የተባለው ጥናት በዘርፉ ከተደረጉ ጥናቶች ትልቁ ሲሆን በኒውዚላንድና በአውስትራሊያ የተደረጉ ትንንሽ ጥናቶችንም አካቷል።

በጀርባዎ ተኝተው መንቃት ችግር ያመጣ ይሆን ?

ማንችስተር በሚገኘው ቅድስት ማርያም ሆስፒታል በሚገኘው የቶሚ ስቲልበርዝ የምርምር ማዕከል የክሊኒክ ዳይሬክተር የሆኑትና ምርምሩንም በዋናነት የሚመሩት ፕሮፌሰር አሌክሳንደር ሔዝል እንደሚመክሩት ከሆነ እርጉዝ ሴቶች በመጨረሻው እርግዝናቸው ሶስት ወራት ወቅት ጋደም በሚሉበት ሆነ በሚተኙበት ወቅት በጎናቸው እንዲሆን ይመክራሉ።

"ድንገት በሚነቁበት ወቅት በጀርባየ ነው የነቃሁት ልጄን ጎድቸዋለሁ ብለው ማሰብ የለባቸውም" የሚሉት ፕሮፌሰሩ

"ዋናው ነገር በየትኛው በኩል እንደሚተኙና እናም ረዥም ሰአት ተኝተው የሚያሳልፉበትን ማወቅ ጠቃሚ ነው" ይላሉ።

"ሰዎች በየትኛው በኩል መንቃት እንዳለባቸው መቆጣጠር ባይችሉም በየት በኩል መተኛት እንዳለባቸው ግን መወሰን ይችላሉ" ብለዋል።

በጎን ለመተኛት የሚጠቅሙ አንዳንድ ነጥቦች

  • ትራስ ወይም ትራሶች በጀርባዎ በኩል መደራረብ በጎን በኩል እንዲተኙ ያበራታታዎታል
  • ድንገት ሌሊት ላይ በሚነቁበት ወቅት አተኛኘትዎን በመገምገም በጎንዎ በኩል ይተኙ
  • ሌሊት ላይ ብቻ ሳይሆን ቀንም ላይ ጋደም በሚሉበት ወቅት አተኛኘትዎን ወደ ጎን በማድረግ ያስተካክሉ
  • በጀርባዎ ተኝተው ድንገት ቢነቁ አይጨነቁ ከብለል በማለት በጎንዎ ይተኙ
  • ጥናቱ በቀኝና በግራ በኩል በመተኛት መካከል ያለውን የአደጋ ልዩነት ግን ማሳየት አልቻለም

ተመራማሪዎቹ በእርግጠኝነት ሞተው የሚወለዱ ፅንሶች ለምን እንደጨመረ በእርግጠኝነት መናገር ባይችሉም ነገር ግን ብዙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እርጉዝ ሴት በጀርባዋ በምትተኛበት ወቅት የሷ ክብደትና ማህፀኗ ልጇን በሚጫኑበት ወቅት የፅንሱን የደም መስመር ስለሚጫነው ደምና ኦክስጅን መተላለፍ ስለሚቸግር ነው።

ከዚሁ ጆርናል የመጡት ኤድዋርድ ሞሪስም አዲሱን የምርምር ስራ "በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነትን እንዳገኘ" ተናግረዋል።

"ይህ ጥናት በጣም ጠቃሚ ነው ምክንያቱም በመጨረሻዎቹ እርግዝና ወቅቶች አተኛኘት የፅንሱን አወላለድ አደጋ ስለሚቀንስ ነው" ብለዋል።

እርጉዝ ሴቶችም በጎናቸው እንዲተኙና አደጋውንም ለመቀነስ የተለያዩ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ነው።

Image copyright Family photo

ሚሼል ኮትል የተባለች የስነ-አዕምሮ ባለሙያ በባለፈው አመት በ37ኛ ሳምንት የእርግዝና ወቅት ፅንሱ ሞቶ የተወለደ ሲሆን ከዛ በፊት ግን ፅንሱ ላይ ችግር እንደነበሩ የሚያሳዪ ምንም አይነት ምልክቶች አልነበሩም።

"ዲር ኦርላ" (ውድ ኦርላ) በሚል ርዕስ ድረ-ገፅ ላይ የምትፅፍ ሲሆን በዚሁ ስር ያለፉ ሴቶችንም ልምድ ታጋራለች።

በአሁኑ ወቅት ሚሼል ጤነኛ ልጅ የወለደች ሲሆን እርጉዝ ሴቶቸ በተግባር ሊተገብሩት የሚችሉትም ምክር ማግኘታቸው በጣም ጠቃሚና ሁሉ ነገር በቁጥጥራቸው ስር እንደሆነ እንዲሰማቸው እንደሚያደርግም ፅፋለች።

"በእውነቱ ከሆነ ሰዎች ጥንካሬ እንዲሰማቸውና ደህንነቱ ለተጠበቀ እርግዝና የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉና የተሻለም ውጤት እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል" በማለት የምትናገረው ሚሼል "ወደኋላ ተመልሼ ሁለተኛ እርግዝናየን ሳስበው በጣም ያስጨንቀኛል ምክንያቱም በፍራቻ የተሞላ ነበር"

" ድንገት የፅንሱ እንቅስቃሴ በሚያቆምበት ወቅት በህይወት ይኑር አይኑር ስለማይታወቅ በጣም አስደንጋጭ ነው"

የሚሼል ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እርጉዝ ሴቶች በሚተኙበት ወቅት ፍራቻ እንደሚሰማቸው ትናገራለች።

"በተለይም ሌሊቱ በጣም አስፈሪ ነው ምክንያቱም ብዙዎች በሚተኙበት ወቅት ፅንሱ እንደሞተ ይሰማቸዋል። መተኛት ግዴታም መሆኑ ሂደቱን አስፈሪ ያደርገዋል" ብላለች።