የኬንያ ፍርድ ቤት የኡሁሩ ኬንያታን አሸናፊነት አጸደቀ

Supreme Court in Nairobi Image copyright AFP

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ወር ተካሂዶ ኡሁሩ ኬንያታ ያሸነፉበተን የድጋሚ ምርጫ አጸደቀ።

ሁለት ቅሬታ አቅራቢዎች ምርጫው ውድቅ እንዲሆን ያቀረቡትን ጥሪ ፍርድ ቤቱ ባለመቀበሉ ኬንያታ በሚቀጥለው ሳምንት ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ።

ፍርድ ቤቱ "በተጽዕኖ ስር" ሆኖ የሰጠው ውሳኔ ነው በሚል የተቃዋሚው ፓርቲ ለአዲሱ መንግሥት ዕውቅና እንደማይሰጥ አስታውቋል።

ለመምርጥ ከተመዘገቡ ሰዎች 39 በመቶዎቹ ብቻ በተሳተፉበት ምርጫ፤ ኬንያታ የ98 በመቶዎቹን ድምጽ በማግኘት ነው ያሸነፉት።

ባለፈው ነሐሴ የተካሄደውን ምርጫ ህጋዊውን መንገድ አልተከተለም በሚል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

የምርጫ ኮሚሽኑ አዲስ ምርጫ አላካሄደም በሚል የድጋሚ ምርጫው በተመሳሳይ ውድቅ እንዲሆን የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት ጠይቀው ነበር።

የስድስቱን ዳኞች ውሳኔ ያቀረቡት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዋና ዳኛ ዴቪድ ማራጋ "ፍርድ ቤቱ ምርጫውን ውድቅ የሚያደርግበት በቂ ምክንያት አላገኘም" ብለዋል።

Image copyright AFP

ከምርጫው በኋላ የነበረው ጊዜ በውጥረት የተሞላ ሆኗል።

ባለፈው ሳምንት የተቃዋሚው ናሽናል ሱፐር አላያንስ (ናሳ) አባላትን ለመበተን ፖሊስ ባደረገው ሙከራ አምስት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

የናሳው ዕጩ ተወዳዳሪ ራይላ ኦዲንጋ የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን የነሐሴውን ምርጫ ስህተቶች አላረመም በሚል ራሳቸውን አግልለው እንደነበር አይዘነጋም።

"ናሳ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በፊትም እንደገለጸው ይህ መንግሥት ህጋዊ አለመሆኑን በተደጋጋሚ በማሳወቅ እንደማንቀበለው ገልጸናል። ይህ አቋማችን በፍርድ ቤቱ ውሳኔ አይቀየርም" ሲሉ የኦዲንጋ አማካሪ የሆኑት ሳሊም ሎኔ ገልጸዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የአሁሩ ደጋፊዎች በተለያዩ የኬንያ ከተሞች ወደ መንገዶች በመውጣት ስሜታቸውን እንዲገልጹ አድርጓል።

የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰዎች ደስታቸውን እየገለጹ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ተቃዋሚዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።