ወደ ሃገራቸው የተመለሱት የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄያቸውን እንደሚያስቡበት አስታወቁ

Saad Hariri arrived in Beirut shortly before midnight on Tuesday Image copyright Reuters

ለሕይወቴ ያሰጋኛል በሚል ሃገራቸውን ጥለው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለጥቆም ወደ ፈረንሳይ አምርተው የነበሩት የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳድ ሃሪሪ ትላንት ምሽት ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ በኋላ የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄያቸውን እንደሚያስቡበት ያስታወቁት።

ሀሃሪሪ እንደተናገሩት የሊባኖሱ ፕሬዚደንት ሚሼል አውን የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄያቸውን ለጊዜው እንዲተውትና ውይይት እንዲያደርጉ ከማከሯቸው በኋላ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሪሪና ፕሬዚደንት ሚሼል አውን ጥልቅ ውይይት እንዳደረጉም ታውቋል።

ሃሪሪ ሥልጣን ለመልቀቅ የተገደዱት በሳዑዲ አረቢያ ግፊት ነው እየተባለ የሚነገረው ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ ተሰምተዋል።

"ፕሬዚደንት ሚሼል አውን የስልጣን መልቀቅ ጥያቄዬን እንዳጤንበትና በምክንያቴ ዙሪያ ውይይት እንዳካሂድ ስለገፋፉኝ ለጊዜው ጥያቄዬን አቆይቸዋለሁ" ሲሉ ከፕሬዚደንት አውን ጋር በሊባኖስ ቤተ-መንግሥት ከነበራቸው ውይይት በኋላ ተናግረዋል።

የሊባኖሱ ፕሬዚደንት ሚሼል አውን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸውን የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ በአካል ካልሆነ አልቀበልም ብለው እንደበር አይዘነጋም።

ዕለተ ቅዳሜ ሃሪሪ ወደ ፓሪስ በማምራት የሊባኖስን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍታት እየጣሩ ካሉት የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑዌል ማክሮን ጋር ተገናኝተዋል።

ሃሪሪ "ረቡዕ በሚከበረው የሊባኖስ የነፃነት ቀን ላይ ተገኝቼ ነው አቋሜን ማሳወቅ የምፈልገው" ሲሉ ፓሪስ እያሉ ተናገረው ነበር።

ሃገራቸው ከተመለሱ በኋላም በአውሮፓውያኑ 2005 የተገደሉት አባታቸው ራፊክ አል-ሃሪሪ መቃብር ሄደው የፀሎት ሥነ-ሥርዓት አካሂደዋል።

ሳድ ሃሪሪ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለጉብኝት በሄዱበት ነበር ለሕይወታቸው በመስጋታቸው ሥልጣን መልቀቃቸውን በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ያሳወቁት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢራን በሊባኖስ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እየገባች ነው፤ ሂዝቦላህ የተሰኘውን ቡድንም እየደገፈች ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

የሊባኖሱ ፕሬዚደንት ሚሼል አውን ሳዑዲ አረቢያ ያለ ሃሪሪ በማስገደድ ሥልጣን እንዲለቁ አድርጋለች ሲሉ ቢወቅሱም ሃሪሪም ሆኑ ሪያድ ኩነናው ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ ይክዳሉ።

ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለቸው የሚነገረው ሃሪሪ የሊባኖስና የሳዑዲ ጥምር ዜግነት ያላቸው ሲሆን በሪያድ ብዙ ንብረት እንዳላቸውም ምንጮች ያሳያሉ።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ