የብርሃን ብክለት፡ በብዙ ሃገራት ለሊቶች እየጠፉ ነው

Night-time scene of UK and part of Western Europe (c) SPL Image copyright Science Photo Library
አጭር የምስል መግለጫ በእንግሊዝ ያለው የለሊት ብርሃን እየጨመረ ነው

የሰው ሠራሽ ብርሃን ስርጭት ከጌዜ ወደ ጌዜ እየተስፋፋ መሆኑን ምድርን በሌሊት ፎቶ በማንሳት የተደረገ አንድ ጥናት ይፋ አደረገ።

እ.አ.አ ከ2012 እስከ 2016 ከቤት ውጭ ያለ የብርሃን መጠን በየዓመቱ በሁለት በመቶ አድጓል።

እንደሳይንቲስቶች ገለጻ ከሆነ በብዙ ሃገራት "ሌሊት መቅረቱ በእጽዋት፣ እንስሳት እና ሰዎች" ላይ አሉታዊ ተፅአኖ እያሳደረ ነው።

የምርምር ቡድኑ ጥናቱን በሳይንስ አድቫንስስ መጽሔት ላይ አሳትሟል።

ጥናቱ በሌሊት ያለውን የብርሃን መጠን የሚለካውን የናሳ ሳተላይት ራዲዮሜትር ተጠቅሟል።

ጥናቱ አንደሚያሳየው በሌሊት ያለው ብርሃን ስርጭት ከሃገር ሃገር ይለያያል። በሌሊት "ከፍተኛ ብርሃን" ያላቸው እንደአሜሪካ እና ስፔን ያሉት ሃገራት ለውጥ አላሳዩም። በደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካ እና አስያ ያሉ ብዙ ሃገራት ግን የብርሃን መጠናቸው አድጓል።

እንደየመንና ሶሪያ ያሉ እና በጦርነት ውስት የሚገኙ ሃገራት ደግሞ በለሊት የብርሃን መጠናቸው ከቀነሱ ጥቂት ሃገራት መካከል ይገኙበታል።

የተለያየ ቅርጽ ያላቸው የለሊት ብርሃኖች ለእይታ የሚማርኩ ቢሆንም በሰዎች ጤና እና በአካባቢ ላይ ተጽእኖ ይኖራቸዋል።

ሰው ሰራሽ ብርሃን "ሰዎች በአካባቢያቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ካመጡ ግኝቶች አንዱ ነው" ሲሉ የጥናት ቡድኑ መሪ ክሪስቶፈር ክይባ አስታውቀዋል።

የምርምር ቡድኑ አባላት በሃብታም ከተሞችና በኢንዱስትሪ አካባቢዎች ያለው ቢጫ ብርሃን ወደ ሃይል ቆጣቢ ብርሃን በመቀየሩ ምክንያት ያለው ደማቅ ብርሃን ይቀንሳል ብለው ጠብቀው ነበር።

"እንደአሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ጀርመን ባሉ እና በተለይም ደማቅ ብርሃን ባላቸው አካባቢዎች ያለው የብርሃን መጠን ይቀንሳል ብዬ ጠብቄ ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ማየት የቻልነው ግን እንደአሜሪካ ያሉት ሃገራት ያላቸው የብርሃን መጠን ባለበት ሲቀጥል እንግሊዝ እና ጀርመን ደግሞ ይበልጥ ብርሃን አግኝተዋል" ብለዋል።

Image copyright NASA
አጭር የምስል መግለጫ እ.አ.አ በ2012 ከተነሳው ይልቅ የ2016ቷ ህንድ ይበልጥ ብርሃን አግኝታለች

ሰዎች የሚያዩትን ሰማያዊ ብርሃን ሳተላይቱ መለየት ሰለማይችል ተመራማሪዎቹ ከገመቱትም በላይ የብርሃን ስርጭቱ ከፍ ብሎ ሊሆን ይችላል።

ሰዎች "በራሳችን ላይ ትክክለኛ ያልሆነ የብርሃን ግዛት እየፈጠርን ነው" ሲሉ የኤክስተር ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ኬቪን ጋስተን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

'አነስተኛ ብርሃን የተሻለ ዕይታ'

"ከለመድነው አንጸባራቂው የማታ ብርሃን ውጭ ተፈጥሮዋዊ የሆነውን የለሊት ብርሃን አውሮፓ ውስጥ ለማግኘት ያስቸግራል" ብለዋል።

የብርሃን ብክለት እየጨመረ መሆኑም አሳሳቢ እንደሆነባቸው ፕሮፌሰር ጋትሰን አስታውቀዋል። "ሰዎች እንዴት አካባቢን እየቀየሩት እንደሆነ ሲታሰብ ለማስተካከል ወይም ወደ ነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል" ብለዋል።

"ከብርሃን ጋር በተያያዘ መወሰድ ያለበት እርምጃ በምንፈልገው ቦታ ብቻ አብርተን ሌላውን ማጥፋት ነው" ብለዋል።

Image copyright NASA
አጭር የምስል መግለጫ ናይልና አካባቢው በምሽት የሚያገኙት ብርሃን እየጨመረ ነው

ከተሞችን አነስተኛ ብርሃን እንዲኖራቸው በማድረግ ለዕይታ እንዳይስቸግር ማድረግ እንችላለን ይላሉ ዶ/ር ክይባ።

"የሰዎች እይታ መሠረቱን ያደረገው በተቃርኖ ነው እንጂ በብርሃን መጠን አይደለም" ሲሉ አስረድተዋል።

'ከቤት ውጭ ያሉ ከፍተኛ መብራቶችን በመቀነስ በአነስተኛ ብርሃን ከፍተኛ ዕይታ እንዲኖር ማድረግ ይቻላል' ብለዋል።

"ይህ ደግሞ ብዙ ሃይል ለመቆጠብ ቢረዳም በሃገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመረጠው አቅጣጫ አይደለም" ሲሉ አስረድተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች