''የተፈጥሮ ሃብታችንን ለመጠቀም የማንንም ይሁንታ አንጠብቅም''

Image copyright Ministry of Foreign Affairs

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም የማንንም ይሁንታ ማግኘት አያስፈልጋትም ብለዋል።

አቶ መለስ ጨምረውም የግብጽ መገናኛ ብዙሃን እና ባለስልጣናት የሚሰጡት መረጃዎች እና አስተያየቶች የግድቡ የግንባታ ሂደት ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ ማሳደር አይችልም ሲሉ ተናግረዋል።

ከቀናት በፊት የግብጹ ፕሬዝዳንት አብድል ፈታ አል-ሲሲ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ግድብ የግብጽን የውሃ ድርሻ ስለሚቀንሰው ለኢትዮጵያ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል ሲሉ የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሕን ዘግበው ነበር።

አል-ሲሲ ማስጠንቀቂያውን ያስተላለፉት ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ካይሮ ላይ ተገናኝተው ግድቡ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት የሚያመላክት ጥናት ማጽደቅ ሳይችሉ በመቅረታቸው እንደሆነ ተነግሯል።

አቶ መለስ የሶስቱ ሀገራት ድርድር ያለ ውጤት የተበተነው ግብጽ የቀኝ ግዛት ስምምነቶችን አሁንም የድርድሩ አካል ይሁን በማለቷ ነው ብለዋል።

ባለፈው ቅዳሜ የዓሳ እርባታ ጣቢያ ምርቃት ፕሮግራም ላይ አል-ሲሲ ተገኘተው ''የግብጽን የውሃ ድርሻ ማንም ሊነካ አይችልም። የኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን የዕድገት ፍላጎት እንረዳለን። ውሃ የሀገራችን የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው። ብሔራዊ ደህንነታችንን ማስጠበቅ ደግሞ አይሳነንም። አራት ነጥብ።'' ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን የግብጹ አልዓረብያ ዘግቧል።

አቶ መለስ ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር የምታደርጋቸውን የትብብር ሥራዎችን አጠናክራ እየቀጠለች የግብጽ ባለስልጣናት እና ተቋማት እያረመዱት ያሉት አቋም ከመርሆቻችን ጋር የሚጣረስ ነው ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች