ሩዋንዳ በሊቢያ 'በባርነት' የተያዙትን ስደተኞች እንደምትቀበል አሳወቀች

The International Migration Organization says it has also gathered evidence of slavery in Libya Image copyright Getty Images

ሩዋንዳ በሊቢያ 'በባርነት'ተይዘው ከሚገኙ አፍሪካውያን ስደተኞች መካከል 30 ሺህ ለሚሆኑት መጠለያ እንደምታዘጋጅ አሳውቃለች።

ሲኤንኤን ባለፈው ሳምንት አፍሪካውያን ስደተኞች ለእርሻ ሥራ በጨረታ ሲሸጡ የሚያሳይ ምስል ከለቀቀ በኋላ ነው ሩዋንዳ ለስደተኞቹ መጠለያ ለማዘጋጀት መወሰኗን ያሳወቀችው።

በሊቢያ እየተካሄደ ያለውን ''የባሪያ ንግድ'' የሚያሳይ ምስል ድንጋጤን ፈጥሯል

"አንድም ያሳለፍነውን በማስታወስ ሌላም አፍሪካውያን እህት ወንድሞቻችን እንደ ከብት ለጨረታ ሲቀርቡ እያየን ዝም ማለት ስለማንችል ነው ይህን ለማድረግ የወሰንነው" ሲሉ የሩዋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሉዊ ሙሺኪዋቦ ተናግረዋል።

በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች በየዓመቱ ሊቢያን አቋርጠው በሜድትራንያን ባሕር በኩል ጉዟቸውን ወደ አውሮፓ ያደርጋሉ።

በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ብዙ መከራና ስቃይ ያልፋሉ፤ እጅግ አነስተኛ በሆነ ዋጋ ለጉልበት ሥራ እስከመሸጥ ድረስ።

"ሶስት ጊዜ ለተለያዩ ነጋዴዎች ተሽጫለሁ"

"ሩዋንዳ እንደ ሌሎች ሃገራት ሁሉ እየሆነ ባለው ነገር እጅግ ተዳናግጣለች። አፍሪካውያን ሴቶች፣ ወንዶች፣ ሕፃናት ሃጋራቸውን ጥለው ተሰደው እንዲህ ዓይነት መከራ ሲደርስባቸው ማየት እጅግ ያስደንግጣል" ብለዋል ሚኒስትሯ።

ሩዋንዳ ትንሽዬ ሃገር ብትሆንም ለችግር ጊዜ የሚሆን ቦታ ግን አታጣም በማለት አክለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ።

"እኔ የማውቀው ሩዋንዳውያን ስደተኞቹን በደስታ እንደሚቀበሏቸው ነው። የሃገሬ ሕዝብ ሰው ወዳድና የተቸገረን የሚረዳ እንደሆነም አውቃለሁ" በማለት ነበር ሚኒስትሯ ኒው ታይምስ ለተሰኘው የሩዋንዳ ጋዜጣ ቃለቸውን የሰጡት።

ሩዋንዳ ጉዳዩን ከዳር ለማድረስ እንዲሁም በሊቢያ ተይዘው ስላሉ አፍሪካውያን ስደተኞች ዕጣ ፈንታ ዙሪያ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ጋር እየመከረች እንደሆነም አሳውቀዋል። ባለፈው ሳምንት የአፍሪካ ሕብረት በሊቢያ እየተከናወነ ባለው የባርያ ሽያጭ እጅግ መደንገጡን አሳውቆ ነበር።

በይነ-መረብ ላይ የተበተነው ምስል ከኒጅር ተሰደው የመጡ ሰዎች ለጉልበት ሥራ በ400 ዶላር (10 ሺህ ብር ገደማ) ለጨረታ ሲቀርቡ ያሳያል።

ወርሃ ሚያዝያ ላይ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ቤት በሊቢያ ባርያ ንግድ እየተከናወነ እንደሆነ መረጃ አለኝ ሲል አስዋውቆ እንደነበር አይዘነጋም።

በሊቢያ የአይኦኤም ተዋካይ ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ስደተኞቹን ይዘው ገንዘብ ካላቸው እሱን ተቀብለው እንደሚለቋቸው ካልሆነ ደግሞ ለሌሎች አሳልፈው እንደሚሸጧቸው ተናግረው ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ