ሊቨርፑል ከቼልሲ. . . ማን ያሸንፍ ይሆን? እነሆ የላውሮ ግምት

ባለፈው የውድድር ዘመን ቼልሲ ከሊቨርፑል ባደረጓቸው የእርስ በርስ ጨዋታዎች የመርሲሳይዱ ሊቨርፑል የተሻለ ሬከርድ ነበረው። በቅዳሜውስ ጨዋታ ማን ያሸንፍ ይሆን?
አርብ
ዌስትሃም ከሌይስተር
የዌስትሃም አዲሱ አሰልጣኝ ዴቪድ ሞዬስ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከዋትፎርደ ጋር አድረገው ሲሸነፉ በዋትፎርደ ሜዳ ተገኝቼ ተመልክቼ ነበር።
የዌስትሃም ተጫዎቾች የልብ መተማመን ወርዶ እንደነበረ ግለፅ ነው።
ከሌይስተር ጋር በሚደረገው ጨዋታ አቻ ቢወጡም ለሞዬስ ጥሩ እነደሆነ አስባለሁ። ሞዬስ በገዛ ሜዳቸው የሚያደርጉት የመጀመሪያ ጨዋታ እንደመሆኑም አንድ ነጥብ ብዙ ዋጋ አለው ብዬ አስባለሁ።
ላውሮ፡ 1 - 1
ዕለተ ቅዳሜ
ክሪስታል ፓላስ ከስቶክ
ዘግይቶም ቢሆን በሮይ ሆጅሰን ታግዞ ለውጥ ማምጣት የቻለው ክሪስታል ፓላስ ወደ አሸናፊነት መመለሱ አይቀሬ ነው።
ነገር ግን ከስቶክ ጋር በሚኖረው ጨዋታ ይህ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም።
ስቶኮች ለተከታታይ ሶስት ጨወታዎች ያለመሸነፍ አሳልፈዋል፤ ጎሎችንም እያስቆጠሩ ይገኛሉ። ለዚህም ነው ለክሪስታል ፓላስ ጨዋታው እንደሚከብድ የማስበው።
ላውሮ፡ 1 - 2
ማንቸስተር ዩናይትድ ከብራይተን
ብራይተን እያሳየ ያለው አቋም ለፕሪሚየር ሊጉ የሚመጥን ክለብ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ባለፈው ሰኞ ከስቶክ በነበራቸውም ጨዋታ ይህንን አሳይተውናል።
ሁለት ጊዜ ተመርተው ሁለት ጊዜ አቻ በመሆን ጥንካሬያቸውን ያሳዩበት ጨዋታ ነበር።
ቢሆንም ብራይተን ወደ ኦልድ ትራፎርድ ሄዶ ነጥብ ይዞ ይመጣል የሚል ተስፋ ብዙም የለኝም።
ላውሮ፡ 2 - 0
ኒውካስል ከዋትፎርድ
ዋትፎርድ ከዌስትሃም ጋር የነበረውን ጨዋታ የተወጣበት መንገድ እጅግ አስገርሞኛል። ኳሱን የያዙበት መንገድ እንዲሁም ወደፊት ሲሄዱ የነበራቸው ቅንጅት በጣም ግሩም ነበር።
ኒውካስል ባለፈው ቅዳሜ በማንቸስተር ዩናይትድ ተሸንፈዋል። ይህም የቤኒቴዝ ቡድን ያጋጠመው ሶስተኛ ተከታታይ ሽንፈት ነው። ለአራተኛ ጊዜ ይህ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም።
ጨዋታው እጅግ ፍልሚያ የሚበዛበት እንደሚሆን እጠብቃለሁ፤ ሀለቱ ቡድኖችም ነጥብ እንደሚጋሩ አስባለሁ።
ላውሮ፡ 1 - 1
ስዋንሲ ከቦርንማውዝ
ስዋንሲዎች አደጋ ላይ ናቸው። ትልቁ ስህተታቸው የነበረውም ሲጉርሰንን ለኤቨርተን በሸጡበት 45 ሚሊዮን ዩሮ ሌሎች ተጫዋቾችን መግዛት አለመቻላቸው ነው። ለቶተንሃም በሸጡት አጥቂያቸው ሎረንቴ ፋንታም ሌላ አጥቂ አለመግዛታቸው አስገርሞኛል።
ቦርንማውዝ በተቃራኒው ካለፉት አራት ጨዋታዎች ሶስቱን ማሸነፍ ችሏል።
ላውሮ፡ 0 - 2
ቶተንሃም ከዌስትብሮም
ዌስትብሮም ቶኒ ፑሊስ ካባረረ በኋላ በተጠባባቂ አሰልጣኙ ጌሪ ሜግሰን እየተመራ ወደ ሜዳ ይገባል። ጌሪ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አልጠብቅም።
ቶተንሃም በፕሪሚየር ሊጉ በአርሴናል ቢሸነፉም በቻምፕዮንስ ሊጉ ዶርትመንድን በማሸነፍ ማንሰራራት ችሏል። ይህንን ጨዋታ ያለምንም ችግር እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።
ላውሮ፡ 2 - 0
ሊቨርፑል ከቼልሲ
ኤደን ሃዛርድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቼልሲ እያሳየ ያለው አቋም እጅግ ምርጥ ሆኗል። ቡድኑ ቼልሲም አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል።
ነገር ግን ሰማያዊዎቹ ወደ ሊቨርፑል ሜዳ ሄደው ነጥብ ይዞ በመምጣት የሊጉን መሪዎች መገዳደር ይጀምራሉ ብዬ አላስብም።
ላውሮ፡ 2 - 1
እሁድ
ሳውዝሃምፕተን ከኤቨርተን
የኤቨርተኑ አጥቂ ኦማር ኒያስ በቅጣት ምክንያት በዚህ ጨዋታ ላይ አይሳተፍም። ኒያስ ቢሰለፍም ኤቨርተን ከሜዳው ውጭ ሄዶ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት የለኝም።
እርግጥ ነው ሳውዝሃምፕተን ጎል ለማስቆጠር እየተቸገረ ይገኛል። ቢሆንም በተጠባባቂ አሰልጣኙ ዳቪድ አንስዎርዝ የሚመራው ኤቨርተን በዚህ ጨዋታ ሊቸገር እንደሚችል ግምቴ ነው።
ላውሮ፡ 2 - 0
በርንሌይ ከአርሴናል
አርሴናል ከሾን ዳይክ ቡድን ጋር የሚኖረውን ጨዋታ እንዴት እንደሚወጣው ለማየት ጓጉቻለሁ። እኩል 22 ነጥብ ላይ የሚገኙት እኚህ ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ እጀግ ማራኪ እንደሚሆንም እጠብቃለሁ።
ባለፈው ሳምንት መድፈኞቹ ቶተንሃምን ባሸነፉበት ጨዋታ ጥሩ ብቃት ላይ የነበረው ሜሱት ኡዚል በዚህስ ሳምንት ምን ያሳየን ይሆን የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው።
ላውሮ፡ 1 - 1
ሃደርስፊልድ ከማንችስተር ሲቲ
ሲቲዎች በሁሉም ውድድሮች 17 ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለዋል። አቋማቸው በጣም ጥሩም ሆነ መካከለኛ ሲቲዎች ጨዋታዎችን እያሸነፉ ነው።
ባለፈው ወር ማንቸስተርን አስተናግደው ጉድ ያደረጉት ሃደርስፊልዶች በሜዳቸው ምን ሊያደረጉ እንደሚችሉ አሳይተውናል። ነገር ግን የማንችስተር ዩናይትድ ስህተትም ታክሎበት እንደሆነ አይዘነጋም። ሲቲዎች ይህንን ስህተት ይደግማሉ ብዬ አላስብም።
0 - 2