ካለሁበት 11፡ እንግሊዝ ሃገር ብቸኝነት ብዙ ሰዎችን ለአእምሮ ሕመም ያጋልጣል

አብዲ ቦሩ Image copyright Abdii Boru

አብዲ ቦሩ እባላለሁ። የሁለት ወንድ ልጆችና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነኝ። አሁን ስልጣን ላይ ባለው መንግሥት በደረሰብኝ በደልና ተደጋጋሚ ውንጀላ ከሃገሬ ወጣሁ።

ሲደርስብኝ የነበረው በደል በሃገሬ ላይ በሠላም ሰርቶ የመኖር መብቴን ስለነፈገኝና እየባሰም በመምጣቱ መጨረሻ ላይ ሁሉን ትቼ የስደት ኑሮ እንድመርጥ አደረገኝ።

ስለዚህ እ.አ.አ በ2006 መጀመሪያ ላይ ሞያሌ ድንበር በማቋረጥ ወደ ኬንያ በስደት ገባሁ።

ለ10 ዓመት ያህል በካኩማ የስደተኞች ካምፕ ስኖር ከቆየሁ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን እና በእንግሊዝ መንግስት በኩል እድል አግኝቼ በ2015 ነሐሴ ደቡባዊ ዮርክሻየር በምትገኘዋ በሼፊልድ ከተማ ባለ ሙሉ መብት ነዋሪ ሆንኩ።

እንግሊዝ ከሃገራችን የሚለያት ትልቁ ነገር ቢኖር የሚታየው እድገት፣ ብልፅግና እና ስልጣኔ ሳይሆን ለሰው ልጅ መብት ያላቸው የላቀ አክብሮት ነው።

ሁሉም ሰው ሃሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብቱ የተጠበቀ መሆኑና በማንኛውም ጉዳይ ዙሪያ ያለአድልኦ እኩል መብት መኖሩ ከሃገራችን በትልቁ እንድትለይ ያደርጋታል።

ሁልጊዜ ሀገሬን እንድናፍቅ ከሚያደርጉኝ ነገሮች አንዱና ዋነኛው የለመድነው ማህበራዊ ኑሮ ነው።

እዚህ አገር ማህበራዊ ኑሮ የሚባል ነገር የለም፡። ከቤተሰብ፣ ከዘመድ እንዲሁም ከጎረቤት ጋር መኖር ወይንም ኑሮን መጋራት የለም።

የምኖረው አፓርታማ ላይ ነው። ፎቅ ላይ ከቤታችን በላይ፣ በታች እና በጎን ሰዎች ይኖራሉ። ሆኖም ግን ከቤታችን ቀጥሎ ያሉትን እንኳ ማን እንደሆኑ አናውቅም፤ እነሱም እንደዚሁ።

በችግር ጊዜም ሆነ በደስታ መጠያየቅ የለም። ሁሉም የየራሱን ኑሮ ይኖራል። ይህንን ማህበራዊ ኑሮ ማጣት ነው እንግዲህ ሃገሬን እንድናፍቅ የሚያደርገኝ።

Image copyright Abdii Boru

ከሼፊልድ ከተማ ዊንተር ጋርደን የሚባለውን ስፍራ እወደዋለሁ።

ይህ የመዝናኛ ቦታ ሁሉን ነገር ያሟላ ነው። በክረምት ወቅት አየሩ በጣም ቀዝቀቃዛ ቢሆንም እዚያ ውስጥ ግን እንዳይቀዘቅዝ ሆኖ የተሰራ ነው። በጣም በሚሞቅበት የበጋ ወቅትም አየሩ ለሰዎች ተስማሚ በሚሆን መልኩ የተዘጋጀ ስፍራ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም የተለያዩ ምስሎችም ይገኙበታል።

ከቤተሰብ ጋር በመሆን የሚዝናኑበትና ምግብ የሚበሉበት ስፍራ አለው። ወደላይ የሚወረወር የውሃ ፏፏቴዎችም አሉት። በተለይ ልጆች የሚሽከረከሩበት የውሃ መዝናኛዎችም አሉት። እነኝህና ሌሎችም ብዙ የመጫወቻና መዝናኛዎች ስላሉት ልጆቼ ይህንን ስፍራ በጣም ይወዱታል። ትምህርት ቤት ሲዘጋና በእረፍት ጊዜያቸው ልጆቻችንን እዚህ እያመጣን እነሱንም ራሳችንንም እናዝናናለን።

ሰብዓዊ መብቱ ተነፍጎ ከሃገሩ በስደት እንደወጣ ሰው ሁሉ እኔም እዚህ አገር በመድረሴ በጣም የሚያስደስተኝ ነገር ቢኖር ለደህንነቴ አለመስጋቴ ነው።

በተጨማሪም ልጆቼ ጥራቱን የጠበቀ ከእድሜያቸውና ከችሎታቸው ጋር የሚመጠጥን ትምህርት ማግኘት መቻላቸው በጣም ያስደስተኛል።

ወደዚህ ሃገር ከመምጣቴ በፊት ለደህንነቴ በጣም እሰጋ ነበር። ምን ይደርስብኝ ይሆን እያልኩም አስብና እጨነቅ ነበር።

በወቅቱ በህይወት ኖሬ ቤተሰቦቼን ተመልሼ አይ ይሆን የሚለው ትልቁ ጭንቀቴ ነበር። ስለዚህ ከዚህ ሃገር ተጠቀምኩ የምለው ደህንነቴ ተረጋግጦ የአእምሮ እረፍት የማግኘቴ ጉዳይ ነው።

አንዳንዴ ከከተማ ውጭ ገጠሩን አቋርጬ ወደ ሌላ ቦታ ስሄድ የማየው ማሳ፣ ስንዴው፣ ገብሱ፣ ከብቶቹ፣ በጎቹ፣ ፈረሶቹ፣ ወንዙ የአባቴ ማሳ፣ ከብቶቹን፣ እንዲሁም የሃገሬን መልከአምድርን እያስታወሰኝ ናፍቆት ይቀሰቅቀስብኛል።

አንድ የተለየ ሃይል ወይም ስልጣን ቢኖረኝ በዚች የምኖርባት ከተማም ሆነ በሌሎች የእንግሊዝ ከተሞች ውስጥ መለወጥ የምፈልገው ነገር መንገዱን ነው።

የዚህ ሃገር መንገድ ጥበት በጣም አሳሳቢ ነው። እዚህ ትንሹም ሆነ ትልቁ በመኪና ነው የሚንቀሳቀሰው። እግረኛ የሚባል ነገር የለም ማለት ይቻላል። በዚህ የተነሳም ወደስራ ለመሄድም ሆነ ከስራ ለመመለስ ረዥም ሰአት ይወስዳል። ስለዚህ የመንገድ ጥበት መለወጥ ብችል ደስ ይለኛል።

Image copyright Abdii Boru

በዚህ ሃገር አስቸጋሪ ነገር ገጥሞኛል የምለው ብቸኝነት ነው። እንደሃገራችን አብሮ መጫወት፣ መነጋገር ፣አብሮ ማሳለፍ በአጠቃላይ ማህበራዊ ኑሮ የለም።

ብቻ መብላት፣ ብቻ መኖር፣ በሃዘንም ሆነ በደስታ ጊዜ ተገናኝቶ አለመነጋገር፣ በተለይም እንደኛ ከሌሎች ሃገሮች ለሚመጡና ማህበራዊ ኑሮን ለለመዱ ከባድ ነው፤ ብቻቸውን ለመጡ ሰዎች ደግሞ ሁኔታው ይብሳል።

ብዙዎች ለአእምሮ በሽታ ተዳርገው ጎዳና ላይ ወዲህና ወዲያ ሲሉ ይታያሉ። ልጆችም በሱስ ተጠምደው ይበላሻሉ፤ አልባሌ ቦታም ይውላሉ።

እኔ እንኳ ፈጣሪ ይመስገን ከቤተሰቦቼ ጋር ስለመጣሁ ለዚህ አይነት ችግር አልተዳረኩም። ሆኖም ግን ማህበራዊ ኑሮ አሁንም ይናፍቀኛል።

የዚህ ሃገር ምግብ አያስደስተኝም። ሁሉ ነገር ቢኖራቸውም ምንም የሚጥመኝ ነገር የለም።

የምግብ አዘገጃጀትና አቀራረቡ አይጥመኝም። ብዙ ጊዜ የነሱ ምግብ ፋስት ፉድ ነው፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንኳ የሚመገቡበት ጊዜ የላቸውም።

ወደ ስራ ቦታ፤ ወደ ቤት ሲሄዱ ወይም መኪናቸው ውስጥ ገዝተው ይመገባሉ። ልጆቼ ግን ፒዛ፣ ዶሮና ድንች ጥብስ መብላት ይወዳሉ።

እኔና ባለቤቴ ደግሞ ከሌሎች የአፍሪካ ሃገሮችና ከአረብ ሃገር በመጡ ሰዎች የሚሰራውን በተለይም "ዙርቢያ" የተባለውን መብላት እንወዳለን።

ከዚህ በቅፅበት ወደ ሃገሬ የሚወስደኝ ነገር ቢኖር ደስ ይለኛል፤ በተለይ ደግሞ የትውልድ መንደሬ አጋርፋ ራሴን ባገኝ በጣም ደስ ይለኛል።

ለጫሊ ነጋሳ እንደነገረው

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦

ካለሁበት 12፡ ''የአውደ ዓመት ግርግር ሁልጊዜ ይናፍቀኛል''

ካለሁበት 13፡ ''ለእኔ ስኬት ማለት ገንዘብ ማግኘት ብቻ አይደለም''

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ