አስገራሚው የደቡብ ኮሪያ ፈተና

የደቡብ ኮሪያ ተፈታኞች Image copyright Chung Sung-Jun

ደቡብ ኮሪያውን በከፍተኛ የትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ወቅት የሚደረጉ አስገራሚ ጉዳዮችን ቢቢሲ ኮሪያ ይፋ አድርጓል።

በየዓመቱ በፈተናው ቀን ደቡብ ኮሪያዊያን ጉዞአቸውን ያዘገያሉ፤ የንግድ ገበያውና ሌሎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ዘግይተው የሚጀመሩ ሲሆን አውሮፕላኖች ደግሞ መነሳትም ሆነ ማረፍ አይፈቀድላቸውም።

ተማሪዎቹ ፈተና ላይ በመሆናቸው መላው ሃገሪቱ እንቅስቃሴዋ ለተወሰነ ጊዜ ይገታል።

ቀኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና የሆነው የኮሌጅ 'ስኮላስቲክ ኤብሊቲ ቴስት' የሚሰጥበት ነው።

ዘንድሮው ፈተና ባለፈው ዓመት እንዲሰጥ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ሃገሪቱን የደቡብ-ምስራቅ የድንበር አካባቢዎችና የፖሃንግ ከተማን በመታው መሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት እንዲራዘም ተደርጓል።

የፈተናው ቀን በተፈጥሮአዊ ምክንያት እንዲቀየር ሲደረግ ዘንድሮው መጀመሪያው ነው።

እንደአሁኑ ዓይነት ችግር በማያጋጥምበትም ወቅት ቢሆን ፈተናው የተሳካ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የኮሪያ መንግሥት ብዙ ሥራዎችን ያከናውናሉ።

ፈተናው እጅግ ከባድ ከሆኑ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናዎች አንዱ ነው።

በረራዎች አይፈቀዱም

በፈተናው ወቅት ከሚከለከሉ ጉዳዮች ቀዳሚው ከአደጋ ጊዜ ውጭ ያሉ አውሮፕላኖች መነሳትም ሆነ ማረፍ አይፈቀድላቸውም።

የበረራ ዕገዳው ተግባራዊ የሚደረገው የእንግሊዝኛ የማዳመጥ ክህሎት ፈተና በሚሰጥበት ጊዜ ሲሆን ለ35 ደቂቃዎች ይቆያል።

በመላው ሃገሪቱ በሚሰጠው ፈተና ላይ ተማሪዎች የእንግሊዘኛ ድምፅም ያለምንም ችግር እንዲሰሙ ለማገዝ የተደረገ ነው።

ፈታኞች በአንድ ቦታ ይቆያሉ

በየዓመቱ ፈተናው ያወጡና ያስተካከሉ እና በተለያዩ ሥራ ደረጃ ላይ የሚገኙ የፈተና ድርጅቱ ሠራተኞች በማይታወቅ ቦታ እንዲቆዩ ይደረጋል።

ይህ ደግሞ ስለፈተናው ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይወጣ ያደርጋል።

እንዲቆዩበት በሚዘጋጅላቸው ቦታም ቢሆን ከማንም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖራቸው ይደረጋል።

ከቤተሰብ ውስጥ ሰው ሲሞት ወይም ሌላ ተመሳሳይ አጣዳፊ ችግር ካልተከሰተባቸው በስተቀር ከሚዘጋጅላቸው ቦታ እንዲወጡ አይፈቀድላቸውም።

በችግር ወቅት እንዲወጡ ሲደረግም የሚንቀሳቀሱበት ቦታ የተገደበ ሲሆን በደህንነት ሰዎችም ክትትል ይደረግባቸዋል።

በዘንድሮው ዓመት ከህዳር 4 ጀምሮ ከሰባት መቶ በላይ የፈተና ድርጅት ባልደረባ ሠራተኞች በተጋጀላቸው ቦታ እንዲቆዩ ተደርጓል። ይህ ማለት ከወር በላይ ከተቀረው ዓለም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም ማለት ነው።

አስቸኳይ ጊዜ አገልግሎቶች

Image copyright Chung Sung-Jun

መረጃ ሾልኮ ከወጣ ወይንም ደግሞ ተማሪው መፈተኛ ክፍሎች ከተዘጉ በኋላ ከመጣ፤ ፈተናውን ደግሞ እንዲወስድ ወይም በሌላ ቀን እንዲፈተን አይፈቀድለትም።

የኮሪያ ብሔራዊ ፖሊስ ድርጅት የዘንድሮውን ፈተና ሁኔታ እንዲከታተሉ 18018 የፖሊስ አባላትን በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች አሰማርቷል።

የእሳት አደጋ ክፍሉ ደግሞ አደጋ መከላከያ መኪናዎችን ከማሰማራት በተጨማሪ ለተማሪዎች ደህንነትና ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስተት የአደጋ ጊዜ መኪናዎችን አሰማርቷል።

ከመደበኛው ጊዜ በቁጥር የሚልቁ ታክሲዎች ለስራ የሚሰማሩ ሲሆን የመንግሥትና የግል መኪናዎች ብዙ ሰዎች ትራንስፖርት በሚጠቀሙባቸው አካባቢዎች ለተማሪዎቹ በተጠባባቂነት ይሰማራሉ።

ባንኮችና የግል ድርጅቶች ዕረፍት ያገኛሉ

በተማሪዎቹ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ችግር ላለመፍጠር በሚል የኮሪያ ምርት ገበያ ስራውን የሚጀምረው ከመደበኛ ሰዓቱ በአንድ ሰዓት ዘግየት ብሎ ነው።

ብዙ የግል ተቋማትም ስራ የሚጀምሩበትን ሰዓት ያዘገያሉ።

ፈተናው ውስብስብ እና ጠንካራ ከመሆኑም በላይ ተፈታኞች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባት አለመግባታቸውን የሚወስን ነው።

ፈተናው "ቀሪውን ህይወት የሚወስን" ተብሎ በብዙዎች የሚገመት ሲሆን መንግስትም ተማሪዎች በፈተናው ቀን ጥሩ ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጥረት ያደርጋሉ።

ተያያዥ ርዕሶች