ሩሲያ በሶሪያ ባደረሰችው ጥቃት 53 ሰዎች ተገደሉ

A still image from video handout shows a Russian long-range bomber hitting targets in Syria on 25 November Image copyright handout via reuters
አጭር የምስል መግለጫ ለዓመታት በዘለቀው ሶሪያ እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ሩሲያ ከፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ጎን ጋር ቆማለች።

ሩሲያ በምስራቅ ሶሪያ በምትገኘው አል-ሻፋህ መንደር ባካሄደችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 53 ሰዎች መገደላቸውን አንድ የታዛቢ ቡድን ገለጸ።

መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው የሶሪያ ሰብዓዊ መብት ታዛቢ ቡድን እንዳለው እሑድ ጠዋት ከተደረገው ጥቃት በኋላ ከሞቱት ሰዎች መካከል 21 ህጻናት ይገኙበታል።

መንደሩ አይ ኤስ በዲር አል-ዙር አካባቢ ከተቆጣጠራቸው ጥቂት ቦታዎች አንዱ ነው።

በመኖሪያ አካባቢዎች በደረሰው ጥቃት 34 ሰዎች መሞታቸውን ታዛቢ ቡድኑ ገልጾ ነበር።

"ቀኑን ሙሉ ፍርስራሾች የማንሳት ስራ ከተከናወነ በኋላ ነው የሟቾች ቁጥር መጨመሩ የታወቀው" ሲሉ ራሚ አብድል ራህማን አስታውቀዋል።

ሩሲያ በበኩሏ በስድስት የጦር አውሮፕላኖች ተጠቅማ በአካባቢው ጥቃት ማድረሷን ብታሳውቅም ዒላማ ያደረገችው የታጣቂዎችን ጠንካራ ይዞታ መሆኑን ጠቁማለች።

ለዓመታት በዘለቀው ሶሪያ እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ሩሲያ ከፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ጎን ቆማለች።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ በአካባቢው ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ የሶሪያ ጦር በጀመረው ጥቃት 120 ሰዎች መሞተዋል

ቀደም ሲል የተካሄዱ የሠላም ውይይቶች ባይሳኩም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያዘጋጀው ውይይት በሚቀጥለው ሳምንት በጄኔቫ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ እሁድ ዕለት በደማስቆ አካባቢ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር በሚገኝ አካባቢ 23 ሰዎች ተገድለዋል። እንደታዛቢ ቡድኑ ገለጻ ከሆነ በምስራቅ ጉታ ከተሞች ከምድር እና ከአየር ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

ሪፖርቶቹን በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም።

በአካባቢው ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ የሶሪያ ጦር በጀመረው ጥቃት 120 ሰዎች መሞታቸው የታዛቢ ቡድኑ አስታውቋል።

ከጦርነቱ በተጨማሪ የ400 ሺህ ሰዎች መኖሪያ በሆነችው ምስራቅ ጉታ ሰዎች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ ነው።

እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ የምግብ እጥረት መኖሩን ተከትሎ ሰዎች የእንስሳት መኖ እና ቆሻሻ በመመገብ ላይ ይገኛሉ።

ተያያዥ ርዕሶች